የኢድ አል-ፈጥር በዓል ቀን የሚወሰነው እንዴት ነው?

ጨረቃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

1445ኛው የኢድ-አልፈጥር በዓል ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 2/2016 በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ የሆነው የረመዳው ወር ሲጠናቀቅ ከፍ ያለ ሃይማኖታዊ ትርጉም የሚሰጠው የኢድ-አልፈጥር በዓል ይከበራል።

በኢድ ዕለት በመላው ዓለም ወዳጅ ዘመድ አምሮ እና ደምቆ ማዕድ ለመቋደስ ይሰባሰባል።

ለመሆኑ በዓሉ የሚከበርበት ቀን የሚወሰነው እንዴት ነው? የቢቢሲው አህመዲን ክዋጃ እንደሚከተለው ያብራራል።

የጨረቃ ጥቅም

የረመዳን መጠናቀቂያ እየተቃረበ ሲመጠ 1.9 ቢሊዮን ሙስሊሞች ጨረቃ መታየት እንድትችል ጥርት ያለ ሰማይ እንዲኖር ይሻሉ።

የረመዳን ወር ጨረቃ ስትታይ እንደሚጀመረው ሁሉ የኢድ ቀን የሚወሰነውም ጨረቃ ስትታይ ነው።

እስልምና የጨረቃ ፍርርቅን መሠረት የሚያደርገውን የሉናር የቀን አቆጣጠር ዘዴን ይከተላል። የረመዳን ወር የሚመጀረው በዘጠነኛው ወር ነው።

በየዓመቱ በሉናር የቀን አቆጣጠር ያለ እያንዳንዱ ወር ከአንድ ዓመት ቀድሞ ከነበረው ወር 11 ቀናት ቀድሞ ይገባል።

በእስልምና የሉናር የቀን አቆጣጠርን መከተል በረመዳን ላይ ለውጥ ስለሚያመጣ ለሙስሊሞች ትልቅ ትርጉም አለው።

ጨረቃን በቴሌስኮፕ ሲመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በረመዳን ወቅት ሙስሊሞች ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ ከምግብ እና ከመጠጥ እራሳቸውን በመቆጠብ ይጾማሉ።

የእስልምና ወራት በፀሐይ የቀን አቆጣጠር ላይ ቢመሠረት ኖሮ በሞቃታማ ወራት ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ረዥም ሰዓት በሚወስድባት የዓለማችን ክፍል ወይም ደግሞ ፀሐይ ለአጭር ጊዜ ወጥታ በምትጠልቅበት ለሚገኙ ሙስሊሞች የረመዳን ወቅት የተለየ ይሆን ነበር።

የኢድ አል-ፈጥር በዓል የሚከበረው በሻዋል አስረኛ ወር የመጀመሪያው ቀን ነው። ይሁን እንጂ ይህ ዕለት መቼ ነው የሚለው በእስልምና አከራካሪ ነው።

አንዳንዶች የሉናር [ጨረቃ] የቀን አቆጣጠርን ሲከተሉ ሌሎች ደግሞ በሥነ ከዋክብት ውስጥ ምልከታዎችን በማድረግ ጨረቃ የምትታይበትን ቀን ይፋ ያደርጋሉ።

አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች ግን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ሥልጣን ያላቸውን እንጂ ግለሰቦች ሰማይን ላይ ተመልክተው የሚሰጡን ሃሳብ አይከተሉም።

የዘንድሮ የኢድ በዓል

የዘንድሮ የ1445ኛው የኢድ በዓል ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 2/2016 እየተከበረ ይገኛል። ይህ ማለት ግን ሁሉም ሙስሊም ኢድን ዛሬ እያከበረ ነው ማለት አይደለም።

በመላው ዓለም የኢድ ቀን ተመሳሳይ ቀን ላይ ውሎ አያውቅም። በአንድ ወይም በሁለት ቀን ልዩነት ይኖረዋል።

ይህ ማለት ሰዎች ከመገኛቸው አንጻር በዓሉን ትናንት ማክሰኞች ያከበሩ ሙስሊሞችም አሉ።

በሉናር ወይም በጨረቃ የቀን አቆጣጠር ሥርዓት አንድ ወር 29 ወይም 30 ቀናት ሊረዝም ስለሚችል ጨረቃን የሚመለከቱ ሰዎችን በፀሐይ መጥለቅ በኋላ ጨረቃ ትታይ እንደሆነ ሰማዩን ይቃኛሉ።

ጨረቃ የምትታይ ከሆነ የኢድ በዓል በቀጣይ ቀን ይደረጋል።

ለኢድ በዓል ሸመታ የወጣች ሴት። በኢንዶኔዢያ ጃካርታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለኢድ በዓል ሸመታ የወጣች ሴት። በኢንዶኔዢያ ጃካርታ

ለምሳሌ የእስልምና መጀመሪያ ተደርጋ በምትወሰደው እና በብዛት የሱኒ ሙስሊሞች መገኘ በሆነችው በሳዑዲ አረቢያ የረመዳን መጀመሪያ እና መጨረሻ ቀን ተደርጎ የሚወሰነው ሰዎች ጨረቃን በዐይን ማየት ሲችሉ ነው።

በሳዑዲ የሚሰጠውን ውሳኔ በበርካታ አገራት የሚገኙ ሙስሊሞች ይከተሉታል።

በሌላ በኩል አብዛኛው ሺአ ሙስሊም በሚኖርባት ኢራን የረመዳን መጀመሪያ እና ማብቂያ የሚወሰነው ጨረቃ በዐይን ከታየች በኋላ ቢሆንም ቁርጥ ያለውን ቀን የሚወስነው ግን መንግሥት ነው።

በኢራቅ ደግሞ የሁለቱም ድብልቅ ተግባራዊ ይሆናል። ሺአ ሙስሊሞች ተጽእኖ ፈጣሪ የእስልምና ሃይማኖት መሪ የሆኑት የአያቶላ አሊ አል-ሲስታኒን መግለጫ ይጠብቃሉ። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሱኒ ሙስሊሞች ደግሞ የራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች የሚሉትን ይሰማሉ።

ቱርክ ደግሞ የረመዳን መጀመሪያ እና መጨረሻን ቀንን የምትለየው የሥነ ከዋክብት ስሌትን መሠረት በማድረግ ነው።

በአውሮፓ የሚገኙ ሙስሊሞች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢያቸው ያሉ የሃይማኖት መሪዎችን ትዕዛዝ ይጠባበቃሉ።