በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ብቅ ጥልቅ የሚሉት ግዙፎቹ “ባዕድ አብረቅራቂ ወጥ ብረቶች”

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የታዩት አብረቅራቂዎቹ ብረቶች

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የታዩት አብረቅራቂዎቹ ብረቶች

በሳምንቱ መጨረሻ በአሜሪካዋ ግዛት ኔቫዳ በረሃ ውስጥ ምሥጢራዊ የሆነ ከአንድ ወጥ የተሠራ አብረቅራቂ ባዕድ የብረት ምሰሶ ቆሞ ታይቷል።

አራት ጠርዞች ያሉት ይህ አብረቅራቂ ብረት ወጥነት ያለው ሲሆን፣ ድንገት ነበር ከሰሜናዊ ላስቬጋስ በአንድ ሰዓት ርቀት ላይ በሚገኘው የኔቫዳ በረሃ የታየው።

ይህ ግዑዝ አካል ረዥም እና ግዙፍ ሲሆን ወጣ ገባ በሆነው በረሃማ ስፍራ ቆሞ ነው የታየው።

ይህንን ምሥጢራዊ ግዙፍ ወጥ ባዕድ የብረት ቅርጽ መጀመሪያ ያዩት የላስ ቬጋስ ፖሊስ አባላት ናቸው።

አስር ጫማ (ሦስት ሜትር) ገደማ እርዝማኔ አለው።

ይህ የብረት ስሪት ምሰሶ መሳዩ ቅርጽ ያለው ባዕድ ነገር በዚህ በረሃ ብቅ ሲል የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ከዚህ ቀደምም እዚያው አሜሪካ ውስጥ በሚገኙት በዩታህ እና በካሊፎርኒያ ግዛቶች እንዲሁም አትላንቲክን ተሻግሮ ዌልስ እና ሮማንያ ውስጥም በድንገተኛ ሁኔታ ታይቷል።

ከምዕራቡ ዓለም በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኬንሻሳ ውስጥም ታይቶ በተቆጣ ሕዝብ ወድሟል።

ከብረት የተሠራው ይህ ግዙፍ ቅርጽ ባዕድ ነገር በመዲናዋ ኬንሻሳ የታየው በአውሮፓውያኑ 2021 ነበር።

ይህ ሲታይ ሦስት ማዕዘን እና አራት ጠርዞች ያሉት የሚመስለው ቅርጽ ከሌሎቹ ረዘም ያለ ሲሆን 12 ጫማ (3.7 ሜትር) ርዝማኔ ነበረው።

ነገር ግን ከየት እንደመጣ ጥርጣሬ የገባቸው የአገሬው ሰው ዝም ብለው አላዩትም። የቻሉ በድንጋይ ደበደቡት ሌሎች ደግሞ እሳት ለኮሱበት።

ይህ ባዕድ መሳይ ብረት ስሪት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብዙ ተብሎለታል።

እምነት ያላቸው ክስተቱን ሰይጣን ተክሎት ይሆናል ብለው ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ደግሞ ምናልባት ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን አስቀምጠውት የሄዱት ነገር ይሆናል ሲሉ መላ ምትም የሰጡ አሉ።

ከዚህ የብረት ቅርጽ ጀርባ ኢሉሚናቲ ሳይኖር እንደማይቀርም ተብሎም ተነግሮ ነበር።

እናም ውስጡ ምን ይዞ ይሆን? የሚል ጥያቄን ያጫረ ነበር። ኮንጓውያኑም ይህንን ባዕድ ነገር ከሰባበሩት በኋላ ውስጡን ሲያዩም የተዘረጉ ብረቶች ብቻ ነበር ያገኙት።

የአካባቢው ከንቲባም የግዙፉን ቅርጽ አመጣጥ ለማወቅ የተወሰኑ ቁርጥራጮችን ወደ ሳይንቲስቶች ላኩ።

ከንቲባው ይህንን ቢያደርጉም የኬንሻሳውን አገረ ገዢ ይህንን ምሰሶ ያቆሙት እኚሁ ከንቲባ ናቸው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ከንቲባው ግን ይህንን አልተቀበሉትም።

እነዚህ ምሥጢራዊ ባዕድ ምሰሶ መሳይ ነገሮች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ ብቅ፣ ጥልቅ እያሉ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

አመጣጣቸውም ሆነ ምንነታቸውም ለበርካታ መላ ምቶች ክፍት ሆኗል።

የሌላ ዓለም ፍጡራን የተከሏቸው፣ የጥበብ ሥራ፣ ሌላም ሌላም ተብሎላቸዋል።

በተለይም ለሳይንሳዊ ልብ ወለድ አድናቂዎች ከሁሉም በላይ አስደማሚ ሆኖ ዘልቋል።

ለመሆኑ እነዚህ ባዕድ ክስተቶች እስካሁን በየትኞቹ የዓለማችን ክፍሎች ታዩ? አመጣጣቸውን በተመለከተ ምን ተብሏል? የሚለውን በዚህ ጽሁፍ እንዳስሳለን።

በኮንጎ አብረቅራቂው ብረት ሲወድም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኮንጎ አብረቅራቂው ብረት ሲወድም

አብረቅራቂ የብረት ቅርጾቹ በየትኞቹ የዓለማችን ክፍል ታዩ?

ዓለም የኮሮናቫይረስ ወረርሽ አስጨንቋት በነበረ ጊዜ ይህ ባዕድ የብረት ቅርጽ በተለያዩ ግዛቶች ታይቷል።

በዚያ ዓለም በጭንቀት ተሰቅዛ በነበረበት ወቅት በአሜሪካ ዩታ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ ግዛቶች ውስጥ እንዲሁም በአውሮፓዊቷ ሮማኒያም ተከስቷል።

ከአስር - አስራ ሁለት ጫማ (ከ3 - 3.7 ሜትር) ርዝማኔ ያላቸው ረዥም፣ ወጥ አብረቅራቂ የብረት ቅርጾች ናቸው።

እነዚህ ነገሮች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ድንገት ብቅ ይሉና ከዚያ ደግሞ ማንም ሳያያቸው ደብዛቸው ይጠፋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ የብረት ቅርጽ የታየው በአሜሪካዋ ዩታህ ግዛት በረሃ ውስጥ ከሦስት ዓመታት በፊት ኅዳር 9/2013 ዓ.ም. ነበር።

በዚያ ስፍራ የቆየውም ለዘጠኝ ቀናት ነበር። ከዘጠኝ ቀናት በኋላም በአውሮፓዊቷ የሮማኒያ ከተማ ፒያትራ ኔምት ብቅ አለ እና በአራተኛው ቀን ደብዛው ጠፋ።

የት ነው ያለው? ሲባል በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኘው የፓይን ተራራ ብቅ አለ፤ እናም ሰዎች በነገታው ካወደሙት በኋላ እንደገና በተከታዩ ቀን ብቅ አለ።

ከሦስት ቀናት በኋላም በኒው ሜክሲኮ ታየ እና እንዲወድም ተደረገ።

ሲታዩ በሌላ ዓለም የሚኖሩ ፍጡራን (ኤሊየን) የሠሯቸው ቅርጾች ይመስላሉ።

ለዚህም ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአውሮፓውያኑ 2001 የተሠራው እና ስለ ጠፈር የሚተርከው ሳይንሳዊ ልብወለድ ‘ስፔስ ኦዲሴይ’ን ስለሚያስታውስ ነው።

በዚህ ፊልም ላይ አሁን እየታዩ እንዳሉት መሳይ ወጥ የሆነ ጥቁር ቅርጽ ይታያል።

በፊልሙ ላይ ይህንን ያስቀመጡት እነዚህ ፍጡራን ናቸው።

ምክንያታቸውም የሰው ልጅ ከአንድ የዝግመተ ለውጥ ደረጃ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሸጋገር ይረዳው ዘንድ በሚል የተቀመጠ መመሪያ ነው።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍል ስለታዩት ወጥ የብረት ቅርጾች ግን ብዙ አይታወቅም።

እርግጠኛ ሆኖ ስለነሱ ማውራት የሚችል አካልም ባለመገኘቱ የዓለማችን አስደናቂነት እና ምሥጢራዊነት መገለጫ አድርጓቸዋል።

በዩታህ የታየው ግዙፉ እና ወጥነት ያለው አብረቅራቂው ብረት

የፎቶው ባለመብት, Utah Department of Public Safety

የምስሉ መግለጫ, በዩታህ የታየው ግዙፉ እና ወጥነት ያለው አብረቅራቂው ብረት

የመጀመሪያው ክስተት

ይህ ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ በዩታህ በረሃ ነበር ብቅ ያለው። ያዩትም በሄሊኮፕተር ላይ ሆነው የአሜሪካ ብርቅዬ የሆኑትን ‘ቢግ ሆርን ሺፕ’ (ቀንዳማ በጎችን) እየቆጠሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው።

ድንገት በበረሃው ውስጥ ግዙፍ የሚያብረቀርቅ ብረታማ ነገር ሲያዩ ሁኔታውን ለመመርመር ወረዱ።

ስፍራው ዳገታማ ሲሆን ያለ ሄሊኮፕተርም ተደራሽ አይደለም።

በመኪናም ሆነ በእግር መሄድ አይቻልም።

እንዴት እንደመጣ ባይታወቅም የጉግል ማፕን በመጠቀም በተገኘው መረጃ ከአውሮፓውያኑ 2015 - 2016 ባለው ጊዜ ተተክሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የዩታህ ግዛት የዚህን አብረቅራቂ ቅርጽ መገኘት ባሳወቀበት የፌስቡክ መረጃው ላይ ኤሊየኖች ያመጡት እንደሆነ ጠቆም አድርጎ ነበር። እንዴት በዚህ በረሃ ላይ ተገኘ የሚለውም ጥያቄ ከዚያ ጀመረ።

ከዘጠኝ ቀናት ቆይታም በኋላ የተለያዩ ህንጻዎችን በመዝለል የሚታወቀው አንዲ ሊውስ እና አስደናቂ ቦታዎችን በማስጎብኘት የሚታወቀው ሲልቫን ክሪስቴንሰን በራሳቸው ፈቃድ ይህንን ቅርጽ አፍርሰው አስወገዱት።

የአካባቢው ሥነ ምኅዳር በሰዎች መጥለቀቅለቅ ይበላሻል በሚል ቅርጹን ማንሳታቸው ከፍተኛ ውዝግብ እና “እናንተ ማን ናችሁ?” የሚል ጥያቄ ያስነሳ ሆኗል።

ሆኖም በዚያው አልጠፋም ሌላ አዲስ ቅርጽ በአውሮፓዊቷ ሮማንያ ውስጥ ብቅ አለ። የታየውም በአርኪኦሎጂያዊ ቦታ አቅራቢያ በሚገኘው ባትካ ዶአምኔይ በተሰኘ አምባ ነው።

በዩታህ ከታየውም በቅርጹ ትንሽ ለየት ያለ ነበር።

ቅርጹ የተገኘበት ከተማ ከንቲባም በሁኔታው ተደስተው፣ ቅርጹን የተውት ታዳጊ ኤሊየኖች ሳይሆኑ አይቀሩም አሉ።

ከተማቸውንም በመምረጣቸው ክብር እንደተሰማቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈው፤ የበለጠ ቱሪስቶች ያመጣልናልም ብለው ተመኙ።

የተመኙት አልሆነም ከአራት ቀናት በኋላ ቅርጹ ደብዛው ጠፋ። እስካሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው።

በሮማኒያ በጠፋበት ዕለት አዲስ ቅርጽ በካሊፎርኒያ በሚገኝ ተራራ ጫፍ በእግረኛ መንገድ ላይ ታየ።

በዚህም የታየው የብረት ቅርጽ ባለ ሦስት ማዕዘን፣ አስር ጫማ ርዝማኔ ያለው እንዲሁም ግማሽ ሜትር ስፋት ነበረው።

በዩታህ እና በሮማኒያ ከታዩት ተመሳሳይ ቁመት ቢኖረውም ስፋቱ ግን ጠበብ ያለ ነው።

ከማይዝግ ብረት (ስቴይንለስ ስቲል) የተሠራው ይህ ቅርጽ በዩታህ በተለየ በመሬት ላይ ጠንካራ መሠረት አልነበረውም።

ጠንካራ ግፊት ሊገለብጠው የሚችል ነበር። ከቀናት በኋላም ለሰዓታት በመኪና የተጓዙ ወንድ ወጣቶች ቅርጹን ደረመሱት።

የትራምፕ አድናቂ የሆኑት እነዚህ ወጣቶች “አሜሪካ ፈርስት [ቅድሚያ ለአሜሪካ]፣ ‘ክርስቶስ ንጉሥ ነው’ የሚል መፈክር እያሰሙ ነበር።

“ከሜክሲኮ የመጡም ሕገወጥ ኤሊየንም ሆነ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራንን አንፈልግም። ክርስቶስ በዚህ አገር ንጉሥ ነው” አሉ።

ቅርጹን ካፈረሱ በኋላ ከእንጨት የተሠራ መስቀል ተከሉ። ሆኖም በነገታው ይሄው ቅርጽ ተመልሶ መጣ።

ከዩታህ እና ከሮማኒያ ቅርጾች በተለየ የካሊፎርኒያውን ግዙፍ ቅርጽ የሠራው ይታወቃል።

የሠሩት ካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው አታስካዴሮ ነዋሪ የሆኑት ትራቪስ ኬኔይ፣ አባቱ ራንዳል ኬኒ፣ ዋድ ማኬንዚ እና ያሬድ ሪድል ናቸው።

እነዚህ ግለሰቦች በብረት የተለያዩ ጥበቦችን የሚሠሩ አርቲስቶች ናቸው።

በሁለቱ ወጥ ቅርጾች የተነሳሱት እነዚህ አርቲስቶች ‘በስፔስ ኦዲሴይ’ ፊልም ላይ ያሉት ሦስት መሆናቸውን በማየት ሦስተኛውን ለሟሟላት ነበር የሠሩት።

ሆኖም ከቀናት በኋላ አራተኛው የብረት ቅርጽ በአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ ግዛት አልቡከርኪ በምትባለው ከተማ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ ታየ።

እሱንም በዚያኑ ቀን ነዋሪዎች በመዶሻ መትተው ደረማመሱት።

በኔቫዳ የታየው አብረቅራቂ ብረት

የፎቶው ባለመብት, Las Vegas Police

የምስሉ መግለጫ, በኔቫዳ የታየው አብረቅራቂ ብረት

ከየት መጡ? የተሰጡ መላምቶች

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የታዩት እነዚህ ቅርጾች ምንጫቸው አንድ አይመስልም። ምናልባትም ሌሎቹ መጀመሪያ የታየው የዩታህ ቅጂ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ይገመታል። የካሊፎርኒያውን የሠሩት የብረት ሥራ አርቲስቶች ናቸው።

ምናልባት ለማስተዋወቂያ የተሠሩ ይሆን? የዩታህ በአውሮፓውያኑ 2020 ቢታይም አምስት ወይም አራት ዓመታት ከዚያ ቀድም ብሎ በዚያ በረሃ ላይ መቆየቱ ይህንን መላ ምት እውነት አያስመስለውም።

ሌላኛው ብዙዎች ያመኑት መላ ምት ደግሞ በዩታህ ዌስት ወርልድ የተሰኘው ተከታታይ ሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም በአውሮፓውያኑ 2015 ከተቀረጸበት አቅራቢያ ከመገኘቱ ጋር ያይዙታል።

የፊልሙ ተዋናዮች እና ሠራተኞች ሆን ብለው ለቀልድ የተዉት ወይም ለፊልሙ ግብዓት እንዲሆን የተሠራ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ሌላኛው መላ ምት ደግሞ እነዚህ ባዕድ የሚመስሉ ቅርጾች የጥበብ ሥራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጸው ነው።

ስለዚህም በዩታህ የተገኘው በአንድ አርቲስት ከተተከለ በኋላ ተከታታዮቹ የዚያ ቅጂዎች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለዋል።

እንዲያ ከሆነ የሠራው አርቲስት ማን ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል።

‘ዘ ሞስት ፌመስ አርቲስትስ’ የተሰኙት የአርቲስቶች ስብስብ የዩታህ እና የካሊፎርኒያን እኛ ነን የሠራናቸው ብለው ነበር። ቡድኑ በድረ ገጹ ላይም ለትክክለኛው ‘የኤሊየን ወጥ ቅርጽ’ በ45 ሺህ ዶላር ሽያጭ አቅርቤያለሁ ሲልም አስተዋወቀ።

ነገር ግን ወዲያውኑ እነ ትራቪስ ኬኒይ የካሊፎርኒያውን ሲገነቡ የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አወጡ። ይህም ‘ዘ ሞስት ፌመስ አርቲስትስ’ እንዳልሠሩት ማረጋገጫ ሆነ።

ምናልባት በዩታህ የነበረውን ሠርተውት ይሆን? ሆኖም የካሊፎርኒያውን እነሱ አለመሆናቸውን ተከትሎ አመኔታን አላገኙም።

ሌላኛው በዩታህ የተገኘው ሠራ ተብሎ የሚገመተው በ2011 (እአአ) ሕይወቱ ያለፈው ቀራጺ ጆን ማክራኬን ነው። በብረት የሚሠራቸው ቅርጾች ከዚህ ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑም ይነገራል።

የሚሠራቸው የብረት ምሰሶ ቅርጾች ‘ስፔስ ኦዲሴይ’ ፊልም ላይ ለተካተቱ ቅርጾች ተጽዕኖ እንዳሳደረም ተናግሮ ነበር። አርቲስቱ በተለያዩ የዓለም ፍጡራን (ኤሊየን) መኖር ያምን የነበረ ሲሆን፣ ሥራዎቹም ከሌላ ዓለም እንደመጡ እንዲመስል ያድርግ ነበር።

አንድ የሥነ ጥብብ ጋዜጣም በዩታህ የተገኘው ቅርጽ ምን ያህል ከአርቲስቱ የቀደመ ሥራ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ዘገበ። የአርቲስቱ ልጅ ፓትሪክ ማክክራከን አባቱ የጥበብ ሥራዎችን በምድረ በዳዎች ላይ በመትከል ሰዎች ድንገት እንዲያዩዋቸው እንደሚፈልግ የማድረግ ራዕይ ነበረው ሲል ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግሯል።

ልጁ ብቻ ሳይሆን የአርቲስቶቹን ሥራዎች ስብስብ የያዘው ዴቪድ ዝዊርነር ጋለሪ ባለቤት የሆነው ዴቪድ ዝዊርነር የዩታህ ክስተት የአርቲስቱ ሥራ እንደሆነ የማያከራክር ነው ሲል ለኒውዮርክ ታይምስ ገልጿል።

አርቲስቱ በዩታህ ምናልባትም በሮማኒያ የተገኙትን ቀርጾ ከሞተ በኋላ ይፋ እንዲሆኑ ምሥጢራዊ መመሪያዎች ሰጥቶ ሊሆን ይችል እንደሆነም ተገመተ።

ሆኖም ግን የዩታህ ምሰሶን ፎቶዎች ዴቪድ ዝዊርነር በቅርበት ከገመገመ በኋላ ጆን ማክክራከን አልሠራቸውም አለ። ምክንያቱም ደግሞ አርቲስቱ ቅርጾቹን ይሠራ የነበረው በእጆቹ ሲሆን የዩታህ ቅርጽ ግን የተገነባው በማሺን መሆኑን በመጥቀስ ነው።

የጥበብ ሥራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም ማን ወይም እነማን ሠሯቸው የሚለው እስካሁን እንቆቅልሽ ነው።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ብቅ ጥልቅ እያሉ የሚታዩት እነዚህ ግዙፍ የብረት ቅርጾች በአስደናቂነታቸው በርካታ መላምቶችን በማስከተል አሁንም አነጋጋሪነታቸው ቀጥሏል።