ኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን ለፍልስጥኤም የአገርነት እውቅናን በይፋ እንደሚሰጡ አስታወቁ

የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማን የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል የሚካሄደውን ንግግር ያግዛል በሚል ለፍልስጥኤም የአገርነት እውቅናን እንደሚሠጡ አስታወቁ።

ስፔን እና አየርላንድ ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት ውሳኔያቸው ከእስራኤል በተቃራኒ በመቆም ወይም ሐማስን በመደገፍ ሳይሆን፣ ሰላምን ለመደገፍ ነው ብለዋል።

እስራኤል በአገራቱ ውሳኔ ላይ ቁጣዋን ገልጻ በአካባቢው የበለጠ አለመረጋጋትን ይፈጥራል በማለት በሦስቱ አገራት ውስጥ ያሉ አምሳደሮቿን ጠርታለች።

ፍልስጤማውያኑ ሐማስ እና ተቀናቃኙ የፍልስጤም ባለሥልጣን የአገራቱን ውሳኔ በአውንታዊነት ተቀብለውታል።

የሦስቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ዛሬ ረቡዕ ይፋ እንዳደረጉት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅናን በመስጠት የሁለት አገራት መፍትሄን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይመን ሃሪስ፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋሀር እና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በሰጡት መግለጫ አገሮቻቸው ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

የስፔን እና የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንደገለጹት አገሮቻቸው በሚቀጥለው ማክሰኞ በይፋ ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅናን ይሰጣሉ።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ በጋዛ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ለፍልስጤም ጥያቄ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ግልጽ አድርጓል ብለዋል።

አክለውም ለፍልስጥኤም አውቅና በመስጠት ‘የሁለት አገራት መፍትሄ’ የፍልስጥኤም አስተዳደርን ማዕከል ማድረግ ለእስራኤልም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍልስጤምን የአገርነት ዕውቅና መስጠት ያለውን ችግር ለመፍታት ብቸኛውን “ጎን ለጎን በሰላም እና በመረጋጋት የሚኖሩ ሁለት አገራት” መፍጠርን ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋሀር የኖርዌይ ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ሌሎችም አገራት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርግ “ጠንካራ መልዕክት ነው” ሲሉ የአገራቸውን ውሳኔ አላማ አስረድተዋል።

የሦስቱ አገራት ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት እርምጃ በአካባቢው አለመረጋጋትን ያባብሳል ስትል እስራኤል ተቃውሞዋን አሰምታለች።

ካርታ

በአገራቱ ውሳኔ የተቆጣችው እስራኤል በአየርላንድ እና በኖርዌይ ላሉት ዲፕሎማቶቿ “ለአስቸኳይ ምክክር” በሚል ጥሪ አድርጋለች።

የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት ለወሰኑት አገራት “ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤ እስራኤል ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑትን እና ደኅንነቷን አደጋ ላይ የሚጥሉትን ከመጋፈጥ አታፈገፍግም” ብለዋል።

ጨምረውም እስራኤል የአገራቱን ውሳኔ በዝምታ እንደማታልፈው እና ከበድ ያለ ውጤት እንደሚያስከትል ገልጸው በተለይ “ስፔን ለፍልስጤም እውቅና መስጠቷን ዕውን የምታደርገው ከሆነ፤ ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ሲሉ አጸፋው በስፔን ያለውን የተገንጣይነት እንቅስቃሴን በተመለከተ ይሁን ወይም ሌላ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

የሦስቱ አገራት ውሳኔ “ለፍልስጤማውያን እና ለዓለም ሽብርተኝነት ውጤት እንዳለው የሚገልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” በማለትም እርምጃው “በአካባቢው የባሰ ሽብርተኝነትን እና አለመረጋጋትን በማስከተል፤ ለሰላም ያለ ተስፋን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጋዛን የሚቆጣጠረው እና በአሁኑ ወቅት ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ሐማስ ሦስቱ አገራት ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸው “በፍልስጤም ጉዳይ ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ አቋም የሚለውጥ ነው” ብሏል።

ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የሆነው ባሲም ናይም ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል በሰጠው ቃል የፍልስጤማውያን “ቆራጥ ትግል” ለአገራቱ ውሳኔ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

በእስራኤል ወረራ ስር የሚገኘውን ከፊል ዌስት ባንክን የሚቆጣጠረው የፍልስጤም አስተዳደር፤ ኖርዌይ፣ ስፔን እና አየርላንድ “ፍልስጤማውያን የዘገየውን ፍትህ እንዲያገኙ የማያወላውል ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል” ሲል ውሳኔያቸውን አወድሷል።

በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተጻፈ ደብዳቤ እንዳመለከተው ቢያንስ 140 የዓለም አገራት ለፍልስጤም ዕውቅናን ሰጥተዋል።

ይህም በተባበሩት መንግሥታት የአረብ አገራት ስብስብ የሆኑትን 22 አገራትን ጨምሮ፣ 57 የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል አገራት እንዲሁም 120 የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ አባላትን ያካተተ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ለፍልስጤም በይፋ ዕውቅናን ካልሰጡ አገራት መካከል የሚገኙ ናቸው።

እስራኤል የፍልስጤምን አገርነት ዕውቅና የማትሰጥ ከመሆኗ ባሻገር ሌሎች አገራትም እንዳይሰጧት ትከላከላለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የሚመራው የውቅቱ የእስራኤል አስተዳደርም በጋዛ እና በዌስት ባንክ ውስጥ የፍልስጤም መንግሥት እንዲቋቋም አይፈልግም።

ለዚህም ምክንያቱ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የፍልስጤማውያን አገር የሚቋቋም ከሆነ ለእስራኤል ኅልውና አደጋ ነው ሲል አጥብቆ ይከራከራል።