የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን በቫቲካን አጸድ ውስጥ 500 ዓመት ያስቆጠረ ንብረት እንዴት አፈራች?

በቫቲካን አጸድ ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርሰትያን 544 ዓመት እንዳስቆጠረ የቫቲካን ከተማ ይፋዊ ገጽ ይገልጻል
የምስሉ መግለጫ, በቫቲካን አጸድ ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርሰትያን 544 ዓመት እንዳስቆጠረ የቫቲካን ከተማ ይፋዊ ገጽ ይገልጻል

ትንሿ ቫቲካን በዓለም ዙሪያ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏት የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዋነኛ መቀመጫ ናት። የዚህችን ከተማ ግማሽ መሬት በሚሸፍነው አጸድ (garden) ውስጥ ከኢትዮጵያ በስተቀር የትኛውም ሀገር የኔ የሚለው ንብረት የለም።

በአጸዱ ከ540 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረች የሚነገርለት የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን ይገኛል። 104 ዓመት ያሳለፈው የኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መንፈሳዊ ኮሌጅም በቫቲካን የሚገኝ ብቸኛው የትምህርት ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ ዓለም ተለይታ በቫቲካን አጸድ እንዴት ንብረት ማፍራት ቻለች? የቢቢሲ አማርኛ ጋዜጠኞች በስፍራው ተገኝተው ጠይቀዋል።

★★★★

የቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በከፍተኛ ደስታ ተውጧል። ከፍተኛ ጭብጨባ እና ሁካታ ይሰማል።

ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች ከግዙፉ ቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ፊት ለፊት ተሰባስበዋል።

በርከት የሚለው ታዳሚ በስልኩ ቅጽበቶችን በማስቀረት ተጠምዷል።

ነጭ ጨርቅ የለበሱ የእንጨት ፍርግርጎች ታዳሚዎች በማገድ፣ በሰዎች መካከል መንገድ ፈጥረዋል።

እነዚህ ፍርግርጎች ላይ ምእመናን የኖሯቸው ጥቂት ሰንደቅ ዓላማዎች ይታያሉ።

በዚህ መንገድ አንድ ሰው ብቻ ይመላለሳል። አንድ ነጭ ተሽከርካሪ ብቻ ይዘዋወራል።

ይህ ልዩ ክፍት ተሽከርካሪ በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ቁጥር አንድ የሆኑቱን ሰው ይዟል።

እኚህ ሰው አቡነ ፍራንሲስ ይባላሉ።

አቡኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ካቶሊካውያን መንፈሳዊ አባት ናቸው።

ብዙ ሃይማኖታዊ ስልጣኖችንም ጨብጠዋል። የእሳቸው ውሳኔ ሚሊዮኖች ላይ ተጽዕኖ አለው።

የሀገረ ቫቲካን መሪም ናቸው። እንዳውም አንዳንዶች በአውሮፓ ምድር ያልተገደበ ፍጹም ስልጣን ያላቸው የሀገር መሪ ናቸው ይላሉ።

ወደ ቡራኬው እንመለስ።

አቡኑ ከነጩ ሃይማኖታዊ ልብሳቸው ላይ ነጭ ካፖርት ደርበዋል። ቆባቸውም እንዲሁ ነጭ ነው።

ጥቁር ሱፍ የለበሱ በርከት ያሉ የግል ጠባቂዎቻቸው ተሽከርካሪውን አጅበዋቸዋል። አይናቸው ለአፍታም ቢሆን ከታዳሚው ላይ አይነቀልም።

ፖፕ ፍራንሲስ፣ ከህመም ጋር እንደሚታገሉ ፊታቸው በግልጽ ይናገራል።

በሰዎች መካከል በተከፈተው መንገድ ከደማቅ ፈገግታ ጋር እጃቸውን እያነሱ ታዳሚውን ይባርካሉ።

ይኼኔ ከፍተኛ ጩኸት እና ጭብጨባ ይሰማል። ታዳሚው በደስታ ሲዋጥ ስሜቱ በቀላሉ ይተላለፋል።

የጤና እክል የገጠማቸው ሰዎች የጳጳሱን ቡራኬ ለማግኘት ሲሞክሩ ይስተዋላል። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ‘ሽኮኮ’አድርገው ጳጳሱን እንዲያይ ያደርጋሉ። የተቀረው ታዳሚ እጁን ከፍ አድርጎ ያጨበጭባል።

በዚህ ስፍራ የቀረ የሰው ዘር ዓይነት ያለ አይመስልም። ዓለም በሙሉ የተወከለችበት አደባባይ ይመስላል።

ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ጥቁር፣ ነጭ - ሁሉም አለ።

ይህቺን ቀን በጉጉት ሲጠቡቁ የቆዩ ይመስላል።

ምክንያቱም ይህ ሁነት ከተከናወነ ድፍን አምስት ወራት ተቆጥሯል።

ከ5 ወራት በኋላ የካቲት 27/2016 ዓ.ም ነበር በዚህ አደባባይ የተገኙት

የፎቶው ባለመብት, Vatican News

የምስሉ መግለጫ, ፖፕ ፍራንሲስ ከ5 ወራት በኋላ የካቲት 27/2016 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጰጥሮስ አደባባይ ቡራኬ ሰጥተዋል

ለወትሮው ይህ ስርዓት የሚከናወነው በየሳምንቱ ረቡዕ ነበር።

ሆኖም የ87 ዓመቱ ሃይማኖታዊ አባት ባጋጣማቸው የጤና እክል ምክንያት ከዚህ ስርዓት ርቀው ቆይተዋል።

ከወራት በኋላ የካቲት 27/2016 ዓ.ም ነበር በዚህ አደባባይ የተገኙት።

ጳጳሱ መባረካቸውን ቀጥለዋል። አንዴ ወደ ቀኝ ሌላ ጊዜም ወደ ግራ እየዞሩ ቡራኬ ይሰጣሉ።

በዚህ መኃል አንዳንዶች እሳቸውን ለማየት በእግራቸው ጣቶች ይቆማሉ። ሌላው በአደባባዩ በተሰቀሉ ግዙፍ ስክሪኖች ይከታተላል።

ቡራኬውን ጨርሰው በከፍተኛ አጀብ ወደ መቀመጫቸው አመሩ። አጭር ጸሎት አድርገው ሌላው ሰርዓት ቀጠለ።

ይህ ሁሉ ስርዓት የሚከናወንበት የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እና ካቴድራል እረፍት የለውም።

ከዚህ የዓለም ካቶሊካውያን ዋነኛ ካቴድራሉ ጀርባ አንድም ሀገር የሌለው ንብረት ኢትዮጵያ አላት።

ወዲዚያ እናቅና!

ለወትሮ ይህ ስርዓት የሚከናወነው በየሳምንቱ ረቡዕ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Vatican News

የምስሉ መግለጫ, ለወትሮ ይህ ስርዓት የሚከናወነው በየሳምንቱ ረቡዕ ነበር።

ከቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ወይም በእነሱ አጠራር ባሲሊካ ጀርባ የቫቲካን አጸድ (Vatican garden) ይገኛል። የትንሿን የዓለም ሀገር ከግማሽ የሚበልጥ መሬት ይህ አጸድ ሸፍኖታል።

ሆኖም ስፍራው ለሁሉም ጎብኚዎች ክፍት አይደለም።

ይህንን አጽድ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ወይም እንደ አደባባዩ ወይም እንደ ትልቁ የቫቲካን ሙዝየም የፈለገ ሁሉ አይጎበኘውም።

የተለየ ፍቃድ ይፈልጋል።

ለስራ ወደ ጣልያን የተጓዘው የቢቢሲ አማርኛ ቡድን ይህንን ስፍራ ለማየት ቀናት መጠበቅ አስፈልጎታል።

የጉብኝቱ ቀን ዕለተ ዕሁድ ነበር።

በዚህ ቀን አቡኑ በሰዎች መካከል አይዞሩም።

ይልቅስ ቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ላይ በምትገኛው ዝነኛዋ በረንዳ ቆመው ቡራኬ እና ትምህርት ይሰጣሉ።

የእኛ ጉብኝት ይህ ሁነት ከሚከወንበት እና በርካቶች ከተሰባሰቡበት አደባባይ ጀርባ ነው - የቫቲካን አጸድ።

የቫቲካን አጸድ (Vatican garden)
የምስሉ መግለጫ, የቫቲካን አጸድ (Vatican garden)

አትክልቶች የፈጠሩት ውብ ምስል፣ ለቁጥር የሚታክቱ የውሃ ፏፏቴዎች (ፋውንቴኖች)፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ጨምሮ ቅዱሳንን የሚወክሉ ሀውልቶች እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ስርዓተ አምልኮ የሚፈጸምባቸው ክፍት ቦታዎች የቫቲካንን አጽድ እጅግ ማራኪ አድርገውታል።

በቫቲካን አጸድ የቀድሞ የርዕሰ ጳጳሳት መኖሪያን ጨምሮ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ ህንጻዎች አሉ።

በዚህ አጸድ ሁሉም ንብረት የቫቲካን ነው - ከሁለት ነገር በስተቀር።

የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን እና የኢትዮጵያ ኮሌጅ።

እነዚህ ተቋማት በቫቲካን የተንጣለለ ቅጥር ግቢ የሚገኙ ብቸኞቹ የውጪ ሀገራት ተቋማት ናቸው።

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኮሌጅ በቫቲካን

ወደ ኮሌጁ አመራን።

ከህንጻው መግቢያ ላይ ለኮሌጁ መመስረት ዋነኛ ሚና የነበራቸውን የፖፕ ቤኔዲክት 15ኛ እና የፖፕፒዮስ 11ኛ ምስሎችን ከበሩ በግራ እና በቀኝ በኩል ተሰቅሏል።

ሰኞ የካቲት 28/2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ሌሎች ኦሬንታል አብያተ ክርስትያናት ዐቢይ ጾም የጀመረበት ዕለት ነው።

በጣልያን እና በሌሎች የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ይህ ጾም ከተጀመረ ከአራት ሳምንት ባላይ አስቆጥሮ ነበር።

በእነዚህ ሀገራት የትንሳኤ በዓል ከተከበረ አንድ ወር አልፏል።

በኢትዮጵያ የአብይ ጾም ከመግባቱ አንድ ቀን ቀድም ብሎ በቫቲካን አጸድ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጳጳሳት ኮሌጅ እየጎበኘን ነው።

የኮሌጁ ተማሪዎች በቀጣዩ ቀን ለሚገባው ጾም እየተዘጋጁ ነው።

ኮሌጁ 104 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ከዚህ ውጪ በቫቲካን ምንም ዓይነት መደበኛ የትምህርት ተቋም የለም።

በአሁኑ ሰዓት ከ22 የማይበልጡ ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት የተውጣጡ አገልጋዮች እየተማሩበት ነው።

ይህ ህንጻ የተማሪዎች ማደሪያ፣ መመገቢያ፣ ቤተ መጻሕፍት እና ስርዓተ ጸሎት የሚከናወንበት አነስተኛ ቤተ መቅደስ ይዟል።

ቤተ መቅደሱ በሮም እምብርት ቫቲካን የሚገኝ አይመስልም።

ገጽታው እና ስርዓቱ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካሉት አቢያተ ክርስቲያናት ጋር አንድ ነው።

ከመግቢያው ፊትለፊት በነጭ መጋረጃዎች የተሸፈኑ የቤተ መቅደሱ ክፍሎች ይታያሉ።

ይህ የኮሌጁ ህንጻ የተማሪዎች ማደሪያ፣ መመገቢያ፣ ቤተ መጽሐፍት እና ስርዓተ ጸሎት የሚከናወንብት አነስተኛ ቤተ መቅደስ ይዟል።

የፎቶው ባለመብት, Bethany Congregation

የምስሉ መግለጫ, ይህ የኮሌጁ ህንጻ የተማሪዎች ማደሪያ፣ መመገቢያ፣ ቤተ መጽሐፍት እና ስርዓተ ጸሎት የሚከናወንበት አነስተኛ ቤተ መቅደስ ይዟል።

በመቅደሱ ግራ በአክሱም ስርወ መንግሰት ጊዜ ወንጌልን የሰበኩት የአቡነ ሰላማ ስዕል ይኛል።

አቡነ ሰላማ ዜግነታቸው ሶሪያዊ ሲሆን “በአቢሲኒያ ምድር” ወንጌልን እንዳስፋፉ ይነገራል።

በግብጽ አሌክሳንድሪያ ከቅዱስ አጥናቴዎስ ጵጵስናን ተቀብለው “በአቢሲኒያ” የመጀመሪያ ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል።

በቫቲካን ኮሌጁ በሚገኘው መቅደስም ያለው ስዕልም ይህንን ይዘክራል።

ከሳቸው ስዕል ከፍ ብሎ በቢጫ መደብ ላይ “ቅዱስ እግዚያብሄር ጸባኦት።” የሚል ጽሁፍ በግዕዝ ፊደላት በቀይ ቀለም ጎልቶ ሰፍሯል።

ከዚህ ፊትለፊት በሌላኛው የመቅደሱ ጥግ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኅበ እግዚአሔር።” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይታያል።

ከመቅደሱ ፊት ለፊት ደግሞ በግዕዝ የተዘጋጁ የጸሎት መጻሕፍት በሁለት አትሮንስ (የመጽሐፍ ማስቀመጫ) ላይ ተዘርግተዋል።

በግራ እና በቀኝ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ቤተ ክርስትያናት የሚታወቁት ከበሮዎች ተቀምጠዋል።

ጸናጽል እና መቋሚያ የመቅዱሱ መገልገያዎች ናቸው።

በኮሌጁ የሚገኙት ተማሪዎች በየዕለቱ በዚህ ስፍራ ቅዳሴን ጨምሮ ሁሉንም ስርዓት በግዕዝ ያከናውናሉ።

አንዳዴም በጣልያንኛ ስርዓተ ቅዳሴ ይደረግበታል።

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኮሌጅ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተማሪዎች በዕለቱ ቅዳሴ ያደርጋሉ
የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኮሌጅ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተማሪዎች በዕለቱ ቅዳሴ ያደርጋሉ

በቫቲካን የሚገኘው ይህ ህንጻ የተማሪዎች ማደሪያ እና መመገቢያ ብቻ ነው።

እዚህ የሚያድሩት ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ተማሪዎች በሮም በሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ይማራሉ።

ተማሪዎች ከኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ የካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት ተመርጠው የተላኩላቸው ናቸው።

በተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በድህረ ምረቃ ፕሮግራም፣ በማስተርስ ዲግሪ ተምረው ይመረቃሉ።

የዶግማ፣ የስነ መለኮት፣ የመጽሀፍ ቅዱስ እና የስርዓተ አምልኮ ጥናት ከትምህርት ዘርፎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሁፎችን ለማጥናት በርካታ ቋንቋዎችን መማር ይጠበቅባቸዋል።

እንደ የትምህርት ዘርፉ ተማሪዎች የላቲን፣ የግሪክ እና ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የአራማይክ (Aramaic) ቋንቋን መማር ግዴታ ይሆናል።

ይህ የኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ኮሌጅ 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር ፖፕ ፍራንሲስ ቦታው ላይ በመገኘት ቡራኬ ሰጥተዋል። ንግግርም አሰምተዋል።

በ2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቫቲካን በነበራቸው ጉብኝት ኮሌጁን ተመልክተዋል።

ይህን ስፍራ በመጎብኘት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው መሪ አይደሉም።

ከዛሬ 54 ዓመታት በፊት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በዚህ ኮሌጅ ተገኝተዋል።

ኃይለ ሥላሴ፣ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ በተሰኘው መጸሐፋቸው በሮም በነበራቸው ቆይታ ቫቲካንን እንደጎበኙ ገልጸዋል።

በዚህ መጸሐፍ ያኔ ለትምህርት የሄዱ ሰባት ኢትዮጵያውያንን ማነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

ንጉሱ በኮሌጁ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር በቫቲካን ራዲዮ ድረገጽ ላይ ተጭኗል።

ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቫቲካን የሚገኘውን የአቢሲኒያ ቤተ ክርስትያን ከጎበኙ በኋላ ያስፈሩት ጽሁፍ

የፎቶው ባለመብት, X/Fitsum Arega

የምስሉ መግለጫ, ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቫቲካን የሚገኘውን የአቢሲኒያ ቤተ ክርስትያን ከጎበኙ በኋላ ያስፈሩት ጽሁፍ

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1962 ዓ.ም ባደረጉት 7 ደቂቃ የፈጀ ንግግር “ኮሌጁን ስንጎበኝ የመጀመሪያችን አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ።

የንግሥና ዘውድ ከመድፋታቸው አስቀድሞ በኮሌጁ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው ይህንን ኮሌጅ ጎብኝተዋል።

“ይኼ [ኮሌጅ] ከተቆረቆረ ጀምሮ የሚመጡ የኢትዮጵያ ልጆች ሀሳባቸው የጠና በመሆኑ የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠራ በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብለዋል።

ቀጥለው በወቅቱ የተቀበሏቸውን የቫቲካን ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛን ለኮሌጁ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋቸዋል።

ንጉሱ ለወቅቱ ተማሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ ደግሞ “በመንፈሳዊ ትምህርት ማመኻኘት ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ትምህርቶች ተምራችሁ ተመልሳችሁም ሀገራችሁን ለማገልገል ማሰብ የሰው ልጅን አንዱ ቁምነገረኛ የሚያሰኘው. . . ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ኃይለ ሥስላሴ ከኮሌጁ በተጨማሪ በዚው አጸድ የሚገኘውን የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን መጎብኘታቸውን በመጻሐፋቸው ገልጸዋል።

ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቫቲካንን በጎበኙበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቫቲካንን በጎበኙበት ጊዜ

ኮሌጅ ውስጥ ካለው መቅደስ ወጥተን ወደ ሌላኛው ክፍል አመራን።

በኮሌጁ ወለል ላይ ከሚገኙ ክፍሎች አንዱ የእንግዶች መቀበያ ነው።

በክፍሉ ኮሌጁን ያስተዳደሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውን ፎቶዎች ተስቅሏል።

በእነዚህ ፎቶዎች መካከል ለዓይን በሚማርክ መልኩ የተዘጋጁ ለክፍሉ ጣሪያ የቀረቡ ሳጥኖች ተደርድረዋል።

ሁለቱ ክፍት ናቸው።

አንደኛው ከኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ የሄዱ መስቀሎች፣ ባህላዊ የዜማ መሳሪያዎች፣ የብራና መጽሐፍትን፣ በክብ ቆዳ ላይ የሰፈረ ስዕል ይዟል።

ስዕሉ ቀልብ ይይዛል።

በቫቲካን የሚገኘው የአቢሲኒያ ቤተ ክርሰትያን የተመሰረት በነጋዴዎች ምክንያት እንደሆነ ይታመናል
የምስሉ መግለጫ, በቫቲካን የሚገኘው የአቢሲኒያ ቤተ ክርሰትያን የተመሰረት በነጋዴዎች ምክንያት እንደሆነ ይታመናል

በኢትዮጵያውያን የአሳሳል ዘይቤ የቀረበ ነው። ነጭ ልብስ የለበሰ አንድ ወንድ እና አንዲት ልጅ የታቀፈች ሴት እንዲሁም ዕቃ የተጫነበት በቅሎ በስዕሉ ይታያል።

ከላይ “ወደ ገበያ ጉዞ” የሚል ጽሁፍ አለው።

በቫቲካን ላለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን እና ኮሌጅ መመስረት ምክንያት የሆኑ ነጋዴዎች የሚዘክር ይመስላል።

ነጋዴዎች እና በቫቲካን ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ምን አገናኛቸው?

የአቢሲኒያ ቤተ ክርስትያን በቫቲካን

በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን ከኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።

ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ካርዲናል ብጹዕ አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ስለ ቤተ ክርስትያኑ አመሰራረት ሲናገሩ ይህንን አረጋግጠዋል።

እንደሳቸው ገለጽ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ከሀገራቸው ተነስተው የሱዳንን እና የግብጽን በረሃ አቋርጠው በግብጽ እስክንድሪያ የሚገኘውን መንበረ ማርቆስ ይሳለሙ ነበር።

ቀጥለው የሲናይ በረሀን አልፈው “ቅድስት ሀገር” ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ይጓዙ ነበር።

ጉዟቸው በዚህ አያበቃም።

የቅዱስ ጳውሎስ እና ጴጥሮስ መካነ መቃብር ለመሳለም ወደ ሮም ጉዞ ያደርጋሉ።

“ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስትያን ገብተን መቃብሩን ተሳልመን የቤተ ክርስትያኑን ውበት አይተን ወጣን” ሲሉ በመጽሐፋቸው ያተቱት አጼ ኃይለ ሥላሴም፣ የቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስን መቃብር ለመሳለም “የኢትዮጵያ መነኮሳት. . . ብዙ ናፍቆት አላቸው እና ከኢትዮጵያ ድረስ ወደ ሮም” ይመጡ እንደነበር ያነሳሉ።

ልብ በሉ፣ የቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር የሚገኘው ከኢትዮጵያ ኮሌጅ እና ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ነው።

በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ወይም ካቴድራል ውስጥ የሚገኘውን ይህንን መቃብር ዛሬም ድረስ ሚሊዮኖች ይሳለሙታል።

በስፍራው በተገኘንበት ጊዜ መቃብሩ ላይ የሚገኘው የቅዳሴ መንበር እድሳት ላይ ነበር።

እንዲያም ሆኖ መካነ መቃብሩ ላይ የሚጸልዩ እና የሚሳለሙ ሰዎች ይታያሉ።

ግዙፉ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በርካታ የጸሎት እና የስርዓተ ቅዳሴ መንበሮች አሉት።

ከሁሉም የከበረው ግን የቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ላይ እንደተገነባ የሚታመነው መንበር ነው።

በካቶሊክ እምነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው እንደ ትንሳኤ እና ልደት (ገና) ያሉ በዓላት ሲከበሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ከዚህ መንበር ሆነው ይቀድሳሉ፣ ቡራኬም ይሰጣሉ።

ግዙፉን ካቴድራል ለመገንባት 120 ዓመታት ፈጅቷል። አሁን 518 ዓመት አስቆጥሯል።

ይህ ካቴድራል በአዘቦት ቀናትም በሰዎች የተጨናነቀ ነው።

ግዙፉ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ቫቲካንን የመሩ በርካታ ጳጳሳት መቃብር ይገኝበታል።

አንድ ነገር ትኩረታችንን ሳበው!

በካቴድራሉ በዛ ያሉ ከእንጨት የተዘጋጁ መንቀሳቀስ የሚችሉ ክፍሎች ይታያሉ።

ከአብዛኞቹ ክፍሎት ላይ ቀይ መብራት ይታያል። እጅግ ጥቂቶቹ ደግሞ አረንጓዴ በርቶባቸዋል።

ጥያቄ ይፈጥራል። ምንድን ናቸው?

ጠየቅን። በኮሌጁ ተማሪ የሆኑ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት “እነዚህ የንስሃ ሳጥኖች ናቸው” አሉን።

የንስሃ ሳጥን ምድን ነው? ለምን አረንጓዴ እና ቀይ መብራት ኖራቸው?

አረንጓዴ መብራት ያለውን እየጠቆሙን “እዛ ውስጥ ካህን ይታያቹኋል?”

“አዎ”

“ካህኑ ‘ንስሃ መግባት የምትፈልጉ ሰዎች ወደ እኔ መምጣት ትችላለችሁ እያሉ ነው’ ካህን ማውራት የሚፈልጉ ሰዎች እሳቸው ጋር ይሄዳሉ ማለት ነው። ጊዜ ያለው ካህን እዚህ ቁጭ ብለው ንስሃ በእንግሊዝኛ ወይም በጣልያንኛ መቀበል ይችላሉ ” አሉን።

ቀይ መብራት ያላቸው ደግሞ በቦታው ላይ ካህን የለም ወይም ሌላ ሰው ንስሃ ላይ ነው የሚለውን ይጠቁማሉ።

ወደ ጉዳያችን እንመለስ።

ይህ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ሁነት ከሌለ በስተቀር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚከፈት ነው።

የፎቶው ባለመብት, X

የምስሉ መግለጫ, ይህ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ሁነት ከሌለ በስተቀር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚከፈት ነው።

“የሀበሻ” ነጋዴዎችም ይህንን ስፍራ ከ15ኛው ክፍል ጀምሮ ይጎበኙት እንደነበር የከተማዋ ይፋዊ የዜና ምንጭ የሆነው ቫቲካን ኒውስ ያትታል።

በአውሮፓውያኑ 1481 የያኔው የካቶሊካውያን ርዕሳነ ሊቀነ ጳጳሳት የነበሩት አቡነ ሲኪስተስ አራተኛ ከአቢሲኒያ የመጡ ነጋዴዎችን አግኝተው አነጋግረዋቸዋል።

ያኔ ከሀበሻ ምድር የሚመጡ ነጋዴዎች ቁጥር የጨመረበት ስለነበር ፖፕ ሲኪስተስ አራተኛ ነጋዴዎቹ ማረፊያ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ሰጡ።

አቡኑ ይህንን ትዕዛዝ ያሳለፉት አንድም አቢሲኒያ ከሮም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራት ሌላም “ሀበሻ ነጋዴዎች ለክርስትና ያላቸውን ታማኝነት በመመልከት እንደሆነ” ቫቲካን ኒውስ አስፍሯል።

ይህንን ትዕዛዝ ካስተላለፉ ከሁለት ዓመታት በኋላ “የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን” ተገንብቶ አለቀ።

በተከታዩ ዓመት ይህ ቤተ ክርስትያን እንዲገነባ ምክንያት የነበሩት አቡነ ሲኪስተስ አራተኛ ህይወታቸው አለፈ።

የሳቸው ህይወት ካለፈ 539 ዓመታት ቢቆጠርም፤ ከሳቸው በኋላ እስከ ፖፕ ፍራንሲስ 265 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቢፈራረቁም የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን ስራው ቀጥሏል።

የቅዱስ ጴጥሮስን መካነ መቃብር ለመሳለም ከበርካታ ሀገራት ከምእመናን እስከ ካህናት ከጥንት ጀምሮ ቢመላለሱም ይህ አይነቱ ቦታ የተሰጠው ለ“ሀበሾች” ብቻ ነው።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰለዚህ ቤተ ክርስትያን ሲጽፉ ወደ ሮም ሲያቀኑ የነበሩት ነጋዴዎች ሳይሆኑ መናንያን ናቸው (መነኩሴዎች) ናቸው ብለዋል “. . .የማረፊያ ስፍራ እየቸገራቸው መጉላላታቸውን አይተው . . . ያኔ የነበሩት ፓፕ (ጳጳስ) ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ለኢትዮጵያ መናንያን ማረፊያ ይሁን ብለው ሰጡ ይባላል” ሲሉ አስፍረዋል።

ከታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ውጪ በአጸዱ የሚገኘው ብቸኛው ቤተ ክርስትያን Stefano degli Abissini ወይም የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው።

የአቢሲኒያ ቤተ ክርስትያን ከግዙፉ ቅዱስ ጴጥሮስ በ136 ዓመታት ቀደም ብሎ ቀደም ብሎ የተገነባ ሲሆን 547 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ቫቲካንን በከበባት ግንብ ውስጥ ይህንን የመሰለ ቤተ ክርስትያን የለም።

በቫቲካን አጸድ ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርሰትያን
የምስሉ መግለጫ, በቫቲካን አጸድ ውስጥ የሚገኘው የአቢሲኒያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርሰትያን

ይህ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ሁነት ከሌለ በስተቀር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚከፈት ነው።

በየዓመቱ ጥር 17 አገልግሎት ይሰጣል።

ይህ ቀን በካቶሊክ ቤተክርስትያን “የዓመቱ እስጢፋኖስ” ተብሎ የሚዘከር ነው።

በዕለቱ በግዕዝ ኢትዮጵያውን እና ኤርትራውያን አገልጋዮች ሰዓታት ይቆማሉ። ማህሌት ያደርሳሉ። ቅዳሴም ይቀደሳል።

‘እንዳለመታደል’ ከዚህ ቀን ጋር ተላልፈናል።

አንዳንዴ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን የቫቲካን ነዋሪዎች በቤተ ክርስትያን ስርዓት ይሞሸሩበታል። ጥምቅት ወይም ሌሎች አገልግሎቶች ይሰጡበታል።

ቤተ ክርስትያኑን ተዘዋውረው የጎበኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “. . . ለኢትዮጵያን መናንያን የተሰጠውን የቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ለማየት ገባን . . .በዚያ ገዳም ያለውን ቤተ ክርስትያን በየማዕዘኑ እየዞርን ስናይ የሰባት ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ስም የተቀረጸባቸውን ጥርብ ድንጋዮች አይተናል” ሲሉ ጽፈዋል።

በአንድ ወቀት አቡነ ፍራንሲስ ስለዚህ ቤተ ክርስትያን ሲናገሩ ይህ ቤተ ክርስትያን የካቶሊክን ዓለምአቀፋዊነትን ይመሰክራል ብለዋል።

ያኔ አቡነ ሲኪስተስ አራተኛ ከአቢሲኒያ ለመጡት ነጋዴዎች የመገልገያ ቤተ ክርስትያን ብቻ ሳይሆን ማረፊያም እንዲሰጥ አዘዋል።

ይህ ማረፊያ ቀስ በቀስ እያደገ ሄዶ አሁን ኮሌጅ ወደ ሆነው ህንጻ ተቀይሯል።

ቫቲካን ኒውስ እንደሚለው ለዚህ ኮሌጅ መመስረት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሁለት ርዕሰ ሊቃነ ጳሳት ናቸው - አቡነ ቤኔዲክት 15ኛ እና አቡነ ፒዮስ 11ኛ።

በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጄ በ1930ዎቹ

የፎቶው ባለመብት, x

የምስሉ መግለጫ, በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጄ በ1930ዎቹ (ከጀርባ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል)

ኮሌጁ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው በ1911 ዓ.ም ነው። ከያኔዋ ኢትዮጵያ ስምንት ተማሪዎች ለትምህርት ተጉዘዋል። ሆኖም ከሀገሩ የአየር ጠባይ ጋር መላመድ ያልቻሉት ተማሪዎች በከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ። የተቀሩት ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለቱ ፖፖች ይህ ኮሌጅ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲገነባ አድርገዋል።

የነጋዴዎቹን ስዕል በተመለከትንበት የእንግዳ መቀበያ ክፍል ጉብኝታችንን አጠናቀቅን። ከዚህ በኋላ አባ ኃይለ ሚካኤል ባራኪ መጥተው ሰላምታ ሰጡን።

ይህ ኮሌጅ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ 18 መሪዎች ተፈራርቀውበታል።

ከዚህ ውስጥ አባ ኃይለ ሚካኤልን ጨምሮ 8 ኤርትራውያን ሲሆኑ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት እነሱ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ 5 ጣልያናውያን፣ 2 ሆላንዳውያን፣ 1 ቤልጄዬማዊ እና አንድ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የአሁኑ አስተዳዳሪ አባ ኃይለ ሚካኤል በደማቅ ፈገግታ ከተቀበሉን በኋላ ጥቂት ገለጸዎችን አደረጉልን። በኤርትራ እና ኢትዮጵያ የዐቢይ ጾም ነገ (ሰኞ የካቲት 28/2016) እንደሚገባ አስታወሱን። ምሳ እንድንበላም ጋበዙን።

ፈገግ ብለው “እድለኛ ናችሁ ዛሬ እንጀራ ነው ያለው” አሉ።

በሮም እምብርት እንጀራ ማግኘት ከባድ ነው። “እድለኛ ናችሁ” ያሉት ለዚያ ይመስላል።

ጥቂት ከቆየን በኋላ ምግብ መድረሱን የሚጠቁም የሚመስል ደውል ሰማን።

ወደ መመገቢያ ክፍሉ ተጓዝን።

የእንጀራው መጠን ሰሃኑን የሚያክል ነው። በጥሩ ሁኔታ የተሰሩ ወጦችም አሉ።

አባ ኃይለ ሚካኤል እና ሌሎች ቀሳውስት ከፊት ለፊት ተቀመጡ። ከእነሱ ግራ እና ቀኝ ደግሞ ሌሎች ተማሪዎች ተደርድረዋል። ከፊት የመመገቢያ ጠረጴዛ ተዘርግቷል።

ከክፍሉ መሃል ከተቀመጠው መደርደሪያ ምግብ እየያዝን ተቀመጥን። ይህንን ግሩም ምግብ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የቫቲካን ሰራተኞች እንዳዘጋጁት ተነገረን። ምግቡን አጣጣምን። እየተገፋ በሚሄድ የምግብ ማቅረቢያ ቡና ቀረበልን። ግሩም ቡና ጠጣን። ከአጭር ጸሎት በኋላ ገበታው ተነሳ።

ይህ ከሆነ ድፍን 55 ቀናት ተቆጠረ። የእምነቱ ተከታዮች ያኔ የተጀመረው ጾም ተጠናቆ ፋሲካን ዛሬ እያከበሩ ነው።

ከ500 በላይ ፋሲካዎችን ያየው የአቢሲኒያ ቤተ ክርስትያን ግን ዛሬም አዲስ መስሎ አለ።

በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጅ በ1930ዎቹ

የፎቶው ባለመብት, x

የምስሉ መግለጫ, በቫቲካን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጅ በ1930ዎቹ