ለ14 ዓመታት ዩናይትድ ኪንግደምን በበላይነት የመራው ወግ አጥባቂው ፓርቲ ለምን ተሸነፈ?

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ ፓርቲ (ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ) ለዓመታት የአገሪቱ ፓለቲካ አድራጊ፣ ፈጣሪ ነበር።

ማሸነፍ ብቻ መለያውም ሆኖ አገሪቱን የመምራት ሥልጣንም የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ብቻ እስኪመስል ድረስ አይነኬ ሆኖ ቆይቷል።

ፓርቲው በተከታታይ አራት ምርጫዎች “ቶሪስ” በመባል የሚታወቁትን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ወደ ሥልጣን አምጥቶ ፖለቲካውን መቆጣጠር ቢችልም በዘንድሮው ምርጫ ያ ግስጋሴ ተገትቷል።

በምርጫው ያሸነፉም ይሁን ያጡ በርካታ የወግ አጥባቂው ፓርቲ ፖለቲከኞች ቃላት አጥሯቸዋል።

በምርጫው መሸነፋቸውንም ገና እያሰላሰሉት ነው።

ፖለቲከኞቹ በአካሄዳቸው እና በአመራራቸው ላይ ምን ችግር እንደተፈጠረ መጻኢ ዕጣ ፈንታቸውስ ምንድን ነው? የሚለው ላይ ገና የጠራ ዕይታም የላቸውም።

ከወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች ጋር በሚደረጉ ንግግሮች አንዳንድ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ይነሳሉ።

አንዳንዶች በምርጫ ያሸነፈው ሌበር ፓርቲ ያቀረባቸው የፖሊሲ አማራጮች ከእነሱ እምብዛም የተለየ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ነገር ግን በዋነኝነት ያሸነፈበት ምክንያት የአመራሮቹ ከዕይታ “ብቃት” ጋር በተያያዘ እንደሆነ ያስባሉ።

ፓርቲው ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አምስት መሪዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ነበሩት።

ዩናይትድ ኪንግደምን ከአውሮፓ ኅብረት ያስወጣት ውሳኔ (ብሬግዚት) እንዲሁም የዓለምን ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ከስር መሠረቱ ያናጋው የኮቪድ ወረርሽኝ ፓርቲው በርዕዮተ ዓለም እንዲከፋፈል አድርገውታል።

አንዳንድ የፓርቲው አባላት ተቃዋሚዎቻቸውን ከመፎካከር ይልቅ እርስ በርስ አንዱ አንዱን ለመጣል በማሴር ጉልበታቸውን ጨርሰዋል። ይህም ሁኔታ አሁንም ገና ያልሻረ ጉዳይ ነው።

የተከሰቱ ቅሌቶችም ፓርቲውን ጥላሸት አልብሰውታል። የኮቪድ መመሪያን ተላልፎ ድግስ ማካሄድ፣ የወሲብ ብልግና እንዲሁም የወለድ ምጣኔን ለመጨመር በሚል የወጣው አነስተኛ በጀት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በቅርቡ የነበረው በምርጫው የሚያሸንፈው ማን ነው? የሚለው የውርርድ ቁማር ውስጥ ገብተዋል መባሉ ዋነኛ ውዝግብ ውስጥ ከቷቸዋል።

ፓርቲው በምርጫው ዘመቻ ወቅት የሥነ ምግባር ችግሮች ታይተውበት እንደሆነ የተጠየቁት የቀድሞው አፈ ጉባኤ ሰር ማርክ ስፔንሰር ሌሎች ፓርቲዎችም ባልተገቡ ባህሪዎች ምክንያት የፓርላማ አባሎቻቸውን እንዳገዱ ጠቅሰዋል።

ነገር ግን በወግ አጥባቂው ፓርቲ ውስጥ በተደጋጋሚ የተከሰተ መሆኑን አምነዋል። በተጨማሪም የሌበር ፓርቲ በምርጫው ዘመቻው ላይ የተጠቀመበት ለውጥም በርካቶች የሚሹት ጉዳይ መሆኑም ተጠቅሷል።

በአገሪቱ የተንሰራፋው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የአገሪቱ የብሔራዊ የጤና ጥበቃን አገልግሎት ወረፋ አድካሚነት እንዲሁም በትናንንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ መራጮች ሲያነሷቸው የነበሩ ጉዳዮች ነበሩ።

ሆኖም ፓርቲው እነዚህን ነገሮች ለማሻሻል የወሰዳቸው እርምጃዎች ሁኔታዎችን እያባባሱ ለመሄዳቸው በርካቶች እየተሰማቸው ነበር።

በተለይም የቀኝ አክራሪው እና ሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪ ናይጀል ፋራጅ ዘግይቶ ወደ ምርጫው ፉክክር መመለስ ጠንካራ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን እና ግብር እንዲቀነስ ለሚሹ መራጮች ፊታቸውን ወደዚህ ፓርቲ በማዞር ሊመርጣቸው የሚችለውን ሕዝብ ከፈለው።

ያንን መራጭም ለመመለስ በሚል በምርጫው ዘመቻ ወቅት ይናገሯቸው የነበሩ ትርክቶች እና ፖሊሲዎች አንዳንድ መካከለኛ አቋም የነበራቸውን መራጮች ሌበር ወይም ሊበራል ዲሞክራቶችን እንዲመርጡ በማድረግ ፓርቲውን ከሁለት ያጣ አደረገው።

እነዚህ ሁኔታዎች ሽንፈት አይቀሬ መሆናቸው ማሳያ ነበሩ? ውጤቱ ያልተጠበቀ አይደለም ማለት ባይሆንም የአንዳንድ የፖለቲከኞችን ድርጊት ማስቀረት ይቻል እንደነበር የሚናገሩ አሉ።

ለምሳሌ ሪሺ ሱናክ አገሪቷ ትልቅ ስፍራ የምትሰጠውን የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መታሰቢያ ዕለት ዝግጅቶችን አለመጨረሳቸው እንደ አሳፋሪ ነገር ነበር የታየው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለእንደነዚህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባራት አዲስ ባይሆኑም፣ ሪሺ እንደ ቦሪስ የመራጮችን ቀልብ መያዝ አልቻሉም።

ቦሪስ በአስራ አንደኛው ሰዓት ዘመቻቸውም ቢሆንም መራጫቸው ቦሪስ፣ ቦሪስ እያለ ስማቸውን ሲጠራ ይሰማ ነበር።

ሌላኛው ሪሺ ሱናክ አገሪቷ የምታደርገው ብሔራዊ ምርጫ በዚህ ወቅት መሆኑን መወሰናቸው እስካሁን ግራ ያጋባ ጉዳይ ነው።

የፓርቲው የምርጫ ዘመቻ መሪ የፓርቲው ፖሊሲዎች ምን ያህል ተፅእኖ እያሳደሩ መሆኑን ለማሳየት መለኪያዎች በሚኖሩበት ወቅት ምርጫው ከመካሄድ እንዲዘገይም ጠይቆ ነበር።

ፓርቲው ያቀረባቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ወይም የወለድ ተመንን መቀነስ የሚሉትን ፖሊሲዎች ተቀባይነትን የመገምገሚያ ጊዜ ያስፈልጋል በሚልም ነበር ምርጫው እንዲካሄድ የተወሰነው።

የዘመቻው መሪ የይዘግይ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞቹ ፖሊሲዎቻቸው በመራጮቻቸው ምን ያህል ቅቡል እንደሆኑ መለኪያ ሳይኖራቸው ነው ወደ ምርጫው ዘው ብለው የገቡት።

ይባስ ብሎ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚያቋርጡ ስደተኞች ቁጥር ጨመረ፣ በእስር ቤቶች መጨናነቅ ምክንያት በርካታ ወንጀለኞች ተፈቱ እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች በገንዘብ እጥረት ቀውስ ተመቱ።

የፓርቲው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

ፓርቲው በምርጫ መሸነፉን ተከትሎ የወግ አጥባቂው (ቶሪ) ተተኪ ለመምረጥ ዝግጅት ከተጀመረ መሪው ሪሺ ሱናክ እለቃለሁ ብለዋል።

ቀጣዩ መሪ ማን ሊሆን ይችላል በሚለውም ላይ በካቢኔው ውስጥ ያገለገሉት እንደ ሰር ኦሊቨር ዶውደን፣ ጄምስ ክሌቨርሊ ወይም ጄሬሚ ሃንት ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ጊዜያዊ መሪ ሊሾም ይችላል እየተባለ ነው።

ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ቀጣዩ የቶሪ አመራር ውድድር እስኪጠናቀቅ ድረስ ሱናክ በፓርቲው የመሪነት ሥልጣን ላይ መቆየት አለባቸው።

የፓርቲው አመራርነትን ለማግኘት ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ድጋፋቸውን ለማሳደግ ሲሰሩ የቆዩ የፓርላማ አባላት አሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ ቀኝ አክራሪ የሆኑት ኬሚ ባዴኖች እንዲሁም መሃል ዘመም የሆኑት ቶም ተገንድሃት ይገኛሉ።

በተጨማሪ የቀድሞው ተፎካካሪዎች ሱኤላ ብራቨርማን እንዲሁም የሱናክ አጋር የነበሩት እና ኋላ ላይ የሰላ ተቺ የሆኑት ሮበርት ጄንሪክም ፓርቲውን ለመምራት ይወዳደራሉ።

የስደተኞችን ጉዳይ በሚመለከተው በአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ሆም ኦፊስ) ያገለገሉት እና የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች የመንግሥቱን የኢሚግሬሽን ጉዳይ ሲተቹም ይደመጣል።

በቀጣዩ ፓርቲውን ማን ሊመራው ይችላል? አባላቱስ ለእነማን ድጋፍ ይሰጣሉ? ፓርቲው ራሱን እንዴት ወደፊት ይቀርጻል? ለሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

የቀኝ አክራሪው ሪፎርም ዩኬ በርካታ መቀመጫዎችን ማሸነፉንም ተከትሎ በዚህ ፓርቲው ያጣውን ድምጽ ለማግኘት ወደ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ያዘነብላል ወይስ ሌላ አማራጮችን ይከተላል? የሚለው በቀጣይ የሚታይ ነው።

አንዳንድ የፓርቲው አባላት የኢሚግሬሽን ፖሊሲያቸው ጠንካራ አለመሆን የውድቀታቸው ዋነኛ ጉዳይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ሌላኛው ደግሞ ሌበር ፓርቲ እንዲያሸንፍ ያደረጋቸውን የፖለቲካ ምኅዳር በማየት ወደዚያ የሚያዘነብሉ የመሃል ዘመም አመራሮችን መምረጥ ይሆናል።

አንዳንድ የፓርቲው አባላት ወግ አጥባቂ ፓርቲው ወደ ቀኝ ዘመምነት ማዘንበል ሊብራል፣ ወግ አጥባቂ መራጮችን እንዳገለለ የሚያምኑ ሲሆን፣ መልሱ ፓርቲው በመጪዎቹ ሳምንታት ራሱን በጥልቀት ፈትሾ በሚያሳልፈው ውሳኔ ላይ የሚታይ ይሆናል።