ፍቅር እስከ መቃብር፡ ደስተኞቹ ባልና ሚስት ስለምን አብረው ለመሞት ወሰኑ?

ጃን እና ኤልስ
የምስሉ መግለጫ, ጃን እና ኤልስ

ጃን እና ኤልስ በትዳር ለአምስት አስርት ዓመታት ገደማ አብረው ኖረዋል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ግን በጃን እና ኤልስ ጥያቄ ዶክተሮች ገዳይ መድኃኒት ከሰጧቸው በኋላ ለአስርት ዓመታት በትዳር አብረው የኖሩት በጋራ ሕይወታቸው አልፏል።

በኔዘርላንድስ በማይድን ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች ሕይወታቸው በፈቃደኝነት እንዲያልፍ የሚፈቅድ ሕግ አለ። ይህ ሕግ ብዙም ባይተገበርም በየዓመቱ በርካታ የደች ጥንዶች ህይወታቸውን በዚህ መንገድ ለማብቃት ይወስናሉ።

ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ የአንዳንድ ሰዎችን ስሜት ሊረብሽ ይችላል።

በፈቃደኝነት የመጨረሻው እስትንፋሳቸው ከመቋረጡ ከሦስት ቀናት በፊት፣ ጃን እና ኤልስ በኔዘርላንድስ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው በፍሪስላንድ ሆነው የመጨረሻ ቀናታቸው እያጣጣሙ ነበር።

ጥንዶቹ እየተንቀሳቀሱ መኖርን የሚወዱ ነበሩ። አብዛኛውን የትዳር ዘመናቸውን ለኑሮ ምቹ ሆኖ በተሰራ መኪና ወይም በጀልባ ላይ አሳልፈዋል።

“አንዳንድ ጊዜ በድንጋይ ክምር ቤት ውስጥ ለመኖር እንሞክር ነበር። ነገር ግን አልሆነም” ሲል ጃን እየቀለደ ይናገራል።

ጃን ዕድሜው 70 ነበር። ያለማቋረጥ የሚያስቃየውን የጀርባ ህመሙን ለማስታገስ እንዲመቸው አንድ እግሩን አጥፎ በሚሽከረከረው መኪና ወንበር ላይ ተቀምጧል።

ባለቤቱ ኤልስ ደግሞ 71 ዓመቷ ነው። የመርሳት በሽታ አለባት። ከአፏ የሚወጡትን አረፍተ ነገሮች አሰካክታ ለመናገር መቸገር ጀምራለች።

ከተቀመጠችበት ተነስታ "ይህ በጣም ጥሩ ነው" ትላለች ወደ ሰውነቷ እየጠቆመች። ወደ ጭንቅላቷ እየጠቆመች ደግሞ “ይህ ግን በጣም ደክሟል" ትላለች።

ጃን እና ኤልስ ትውውቃቸው የሚጀምረው ገና ጨቅላ እያሉ በመዋዕለ ሕፃናት ነበር።

በዛ የሕይወት ዘመን ትስስራቸው ጀመረ። ጃን በወጣትነቱ ለኔዘርላንድ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ሆኪ ተጫውቷል። በኋላ አሰልጣኝ ሆነ።

ኤልስ ደግሞ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት ሰልጥናለች። ሁለቱን ጥንዶች አንድ ያደረጋቸው ግን ለውሃ እና ለጀልባ እና ለጀልባ ጉዞ ያላቸው የጋራ ፍቅራቸው ነው።

ጥንዶቹ ወጣት ሆነው ይኖሩ የነበረው እንደቤት በሚያገለግል ጀልባ ላይ ነበር። በኋላም ዕቃ የሚጭን ጀልባ ገዙ። በኔዘርላንድስ የተለያዩ አካባቢዎች እቃዎችን የማጓጓዝ ሥራ ጀመሩ።

ጥንዶቹ ብቸኛውን ልጃቸውን ወለዱ። ልጃቸው አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ። ልጆቹ ከወላጆቹ ጋር የሚያሳልፈው ቅዳሜና እሁድን ብቻ ነበር።

በእረፍት ወቅት ልጃቸው አብሯቸው ጀልባውን ይሳፈር ጃን እና ኤልስ ሊጎበኟቸው ወደሚችሏቸው ወደ አስደሳች ቦታዎች ይጓዛሉ።

እአአ በ 1999 የጭነት ሥራው ፉክክር በዛበት። ጃን ከአስር ዓመታት በላይ የሰራው ከባድ የጉልበት ስራ ለጀርባ ሕመም ዳርጎታል።

ጃን በ 2003 የጀርባ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት። ግን አልተሻለውም። የሕመም ማስታገሻ መውሰዱን አቆመ። ከባድ ሥራም መስራት አልቻለም። ኤልስ ግን በማስተማር ሥራዋ ተጠምዳለች።

ጥንዶቹ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በማይድን በሽታ ከመሰቃየት ይልቅ በሐኪሞች ድጋፍ በፈቃደኝነት ሕይወትን ስለማሳለፍ ጉዳይ ያወጋሉ።

ጃን ከአካላዊ ጉዳቱ ጋር ረጅም ጊዜ መኖር እንደማይፈልግ ለቤተሰቡ ያስረዳል። ጥንዶቹም ኤንቪቪሲ የተባለውን የኔዘርላንድን "የመሞት መብት" ተቋም ተቀላቀሉ።

"ብዙ መድሃኒት እየወሰዱ መኖር ሕይወት አይደለም። መኖር አይባልም”ይላል ጃን። "ስለዚህ በእኔና በኤልስ ሕመም ምክንያት ይህን ማቆም ያለብን ይመስለኛል።"

ጃን “ይህን ማቆም” ሲል መኖርን ማቆም አለብን ማለቱ ነው።

ጃን እና ልጃቸው
የምስሉ መግለጫ, ጃን ከብቸኛው ወንድ ልጃቸው ጋር

እአአ 2018 ኤልስ ከማስተማር ሥራዋ ጡረታ ወጣች።

የመርሳት ምልክቶችን እያሳየች ነበር ቢሆንም ሐኪም ቤት ለመሄድ አልፈቀደችም። በኋላ ላይ የሕመም ምልክቶቿ ችላ ሊባሉ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ።

እአአ በ2022 የመርሳት በሽታ እንዳለባት የታወቀ ዕለት ኤልስ ባሏን እና ልጇን ትታ ከሐኪሙ ክፍል በብስጭት ወጣች።

ኤልስ ሕመሟ እንደማይሻሻል ካወቀች በኋላ ነበር ከባለቤቷ እና ከልጇ ጋር በፈቃደኝነት ስለመሞት መወያየት የጀመረችው።

በፈቃደኝነት ጥያቄ ካቀረበ በሕጋዊ ሁኔታ በሐኪም እገዛ ራስን ማጥፋት እና በሐኪም ሕይወትን ማጥፋት ህጋዊ ናቸው።

በኔዘርላንድስ አንድ ሰው አካላዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ሕመም አጋጥሞት ታማሚው ሕመሙን መቆጣጠር የማይችለው እና ሕመሙ የማይድን ከሆነ በሕኪሞች ይሁን እና ድጋፍ በታማሚው ጥያቄ ሕይወት ሊቋረጥ ይችላል።

እአአ 2023 በኔዘርላንድስ 9 ሺህ 68 ሰዎች በዚህ መልኩ ሞተዋል። በ2023 በሕመም ይሰቃዩ የነበሩ 33 ያህል ጥንዶች በፈቃደኝነት በጋራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል።

በሮተርዳም በሚገኘው የኢራስመስ ሕክምና ማዕከል የሥነ ምግባር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሮዝመሪን ቫን ብሩኸም "ብዙ ዶክተሮች የመርሳት ችግር ላለባቸው ታካሚዎች በፈቃደኝነት መሞትን ለመፍቀድ አይደለም ለማሰብ እንኳን አይፈልጉም" ብለዋል ።

ይህን ሃሳብ የጃን እና የኤልስ ሐኪምም ይጋሩታል።

ኤልስ

የፎቶው ባለመብት, Els van Leeningen

የምስሉ መግለጫ, ኤልስ በእአአ 1960ዎቹ መጨረሻ

ሐኪማቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ጃን እና ባለቤቱ በፍቃደኝንት ሕይወታቸውን ለማቋረጥ የፈቀዱ ጥንዶችን ወደሚያዘጋጅ ክሊኒክ ፊታቸውን አዞሩ።

ተቋሙ ባለፈው ዓመት በኔዘርላንድ በጋዛ ፍቃዳቸው ሕይወታቸው ካለፉት መካከል 15 በመቶ የሚሆኑ አስፈጽሟል።

ጥንዶች ሕይወታቸውን ባጋራ ለማጥፋት የሚፈልጉ ከሆነ፣ የሕክምና ባለሙያዎች አንዱ አጋር በሌላው ላይ ተጽዕኖ አለማሳደሩን እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል።

ዶ/ር በርት ኬይዘር ከዚህ ቀደም በጋራ ሕይወታችን እንዲያበቃ እንፈልጋለን ያሉ የሁለት ጥንዶች ጉዳይን ተመልክተዋል።

ባል ሚስቱን እያስገደደ እንደሆነ የጠረጠሩበት እና ባልና ሚስት አብረው ለመሞት የጠየቁበትን አጋጣሚም ያስታውሳሉ። ዶክተር ኬይዘር ሚስትን ብቻዋን ባነጋገሩ ወቅት፤ “በጣም ብዙ ዕቅድ እንዳላት ተናገረች…!" ይላሉ ዶክተር ኬይዘር።

ባሏ በጠና መታመሙን በግልጽ ብትናገርም ከእሱ ጋር የመሞት እቅድ እንደሌላት ከተናገራች በኋላ የሁለቱ ጥንዶች አብሮ የመሞት ሒደቱ እንዲቋረጥ ተደረገ። ባል በተፈጥሮ ምክንያት ህይወቱ አለፈ። ሚስት አሁንም በህይወት አለች።

በፕሮቴስታንት ቲዎሎጂካል ዩኒቨርሲቲ የጤና ስነምግባር ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ቴዎ ቦር በኔዘርላንድስ የሚደረገውን የፈቃደኝነት ሞት በይፋ ከሚተቹት አንዱ ናቸው።

“በሐኪም መገደል ትክክል ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ለየት ባሉ ሁኔታዎች ብቻ መሆን አለበት” ብለዋል።

ዶ/ር ቦርን የሚያስጨንቃቸው የጥንዶች በጋር መሞት ተጽእኖ ነው። በተለይም ከኔዘርላንድስ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አንዱ እና ባለቤታቸው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አብረው መሞትን ከመረጡ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን ስበው ነበር።

"ባለፈው ዓመት በርካታ የጥንዶች ሞት ነበሩ። አብሮ መሞትን እንደ ጀግንነት የመቁጠር አዝማሚያ አለ" ብለዋል ዶክተር ቦር።

ኤልስ እና ጃን በሠርጋቸው  ቀን
የምስሉ መግለጫ, ኤልስ እና ጃን በሠርጋቸው ቀን እአአ 1975

ጃን እና ኤልስ የያዛቸው በፍጥነት እንደማይገድላቸው ቢያውቁም በሕመሙ እየተሰቃዩ መኖርን ግን ጨርሶ አልፈለጉትም።

ጃን “ሕይወቴን ኖሬያለሁ። ከእንግዲህ ሥቃይ አልፈልግም። እያረጀን ነው። ስለዚህ መቆም ያለበት ይመስለናል” ይላል።

“ልጃችን ጤናችንን ሊያሻሽል የሚችል ‘የተሻለ ጊዜ፣ የተሻለ ሁኔታ ይመጣል’ ይለናል። ለእኔ ግን ይህ አይታየኝም” ብሏል ጃን።

ኤልስም ተመሳሳይ ስሜት አላት።

"ሌላ መፍትሄ የለም።"

ከመጨረሻው ቀጠሯቸው አንድ ቀን በፊት ኤልስ፣ ጃን፣ ልጃቸው እና የልጅ ልጆቻቸው አብረው ነበሩ።

"ከእናቴ ጋር በባህር ዳርቻ ላይ በእግር ለመጓዝ ሄድኩ። ልጆቹ ይጫወቱ ነበር። … በጣም እንግዳ ቀን ነበር” ይላል ልጃቸው።

"ማታ ላይ እራት እየበላን እንደነበር አስታውሳለሁ። እናም ሁላችንም ያንን የመጨረሻ እራት አብረን ስንበላ እያየሁ እንባዬ ፈሰሰ" ብሏል።

ሰኞ ጠዋት ሁሉም ሰው በአካባቢው በሚገኝ ሕክምና ማዕከል ተሰባሰበ። የጥንዶቹ የቅርብ ጓደኞች ነበሩ። የጃን እና የኤልስ ወንድሞች እና ዘመዶቻቸውም ተገኝተዋል።

"ዶክተሮቹ ከመምጣታቸው በፊት ሁለት ሰዓት አብረን አሳለፍን። ስለ ላለፉት ትውስታዎቻችን አወራን… ሙዚቃም አዳመጥን" ብሏል።

ባልና ሚስት የሚወዷቸውን ሙዚቃዎች ሲያደምጡ።

“የመጨረሻው ግማሽ ሰዓት አስቸጋሪ ነበር። ዶክተሮቹ መጡ፤ ሁሉም ነገር በፍጥነት ተከናወነ። የሚያዘጋጁትን አዘጋጅተው ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቀሩ” ይላል ልጃቸው።

ኤልስ ቫን ሊኒንገን እና ጃን ፋበር በዶክተሮች ገዳይ መድኃኒት ተወጉ። በሰኔ 3/2024 ጥንዶቹ አብረው ሞቱ።

የመኪና ላይ ቤታቸው አሁንም ድረስ ለሽያጭ አልቀረበም። የኤልስ እና የጃን ልጅ ለጥቂት ጊዜ አቆይቶ ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር ለእረፍት ሊሄዱበት አቅዷል።