በሱዳን ያንዣበበውን የዘር ማጥፋት ዓለም ችላ እንዳለው የተመድ ባለሙያ ተናገሩ

ዳርፉር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሱዳን ዳርፉር ግዛት የዘር ማጥፋት እያንዣበበ ቢሆንም የዓለም ትኩረት ግን የዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት ላይ ብቻ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያ ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊን የዘር ማጥፋትን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ የሚያማክሩት ልዩ ልዑክ አሊስ ዋይሪሙ ንደርቱ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በዳርፉት የዘር ማጥፋት የተካሄደበት ወይም ሊካሄድ የሚችልበት ሁኔታ አለ።

በሱዳን ኤል ፋሽር ከተማ ውስጥ ሰዎች በጎሳ ማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን ባለሙያዋ ተናግረዋል።

በከተማው የሚገኝ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ተቋም ባለፉት 10 ቀናት 700 ሰዎች መገደላቸውን መዝግቧል።

ከዳርፉር ግዛት በሱዳን ጦር ሥር የሚገኘው ብቸኛ ከተማ ኤል ፋሽር ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት ጦርነቱ ተባብሷል።

ፈጥሮ ደራሽ ኃይሉ እና የሱዳን ጦር ከአንድ ዓመት በላይ ጦርነት ውስጥ ሲሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተድለዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተሰደዋል።

ኢብራሒም አል-ታይብ አለ-ፋኪ የተባለ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ እህቱ የተገደለችው ቤታቸው ላይ በተፈፀመ የአየር ጥቃት ነው።

ሦስት ልጆቹ ከአያታቸው ጋር እንዲቆዩ ቢልካቸውም ይህ ቤትም በአየር ጥቃት እንደወደመ ገልጿል። አሁን መላ ቤተሰቡ መጠለያ ውስጥ ይገኛል።

“በኤል ፋሽር ምንም ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም” ብሏል።

የተመድ ባለሙያ እንደተናገሩት ሁኔታው “እንደ ሩዋንዳ” እየሆነ ነው።

“በኤል ፋሽር ጥቃት እየተባባሰ ነው። ግጭቱ አስጊ ደረጃ ላይ ይገኛል። ድምጼን ለማሰማት ብሞክርም ትኩረት ያለው በዩክሬን እና ጋዛ ጦርነቶች ላይ ስለሆነ ሰሚ አላገኘሁም” ብለዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋችም በዳርፉር የዘር ማጥፋት ስጋት እንዳለ አስታውቋል።

በማሳሊት ብሔር እንዲሁም አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማጽዳትና ሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

የመብት ጥሰቱን እየፈፀሙ ይገኛሉ ያላቸው የፈጥኖ ደራሽ መሪው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሚቲ)ን ጨምሮ ሌሎችም ኃይሎች ተጠያቂ እንዲደረጉም ጠይቋል።

አረብ ያልሆኑ አርሶ አደሮችና አረብ አርብቶ አደሮች መካከል ለረዥም ጊዜ የቆየ ቁርሾ ያለ ሲሆን፣ ጦርነቱ ውጥረቱን አባብሷል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋ ላይ ከበባ ከማድረጉም ባሻገር የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።

ተመድ እንደሚለው አምና በዳርፉሯ ኤል ጀኒና ከተማ ወደ 15 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።

የምዕራብ ዳርፉር አገረ ገዢ ካሃሚስ አባካር ባለፈው ሰኔ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በዘር ማጥፋት ከከሰሱ ከሰዓታት በኋላ መገደላቸው ይታወሳል።

ፈጥሮ ደራሽ ኃይሉ እየተከሰተ ያለው “የብሔር ግጭት ነው” ይላል።

ለዚህ ቡድን መነሻ የሆነው የጃንጂዋድ ሚሊሻ ቡድን ዳርፉር ውስጥ አረብ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ባነጣጠረ የዘር ማጥፋትና የዘር በማጽዳት ወንጀሎች በ2003 ተከሷል።