የተመድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል በራፋህ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት እንድታቆም አዘዘ

የአይሲጄ ዳኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በአስቸኳይ እንድታቆም ውሳኔ አስተላለፈ።

የአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) ውሳኔ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመችው ያለውን የዘር ማጥፋት ለመግታት በርካታ እርምጃዎች እንዲወሰዱባት ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት ያቀረበችውን ማመልከቻ የደገፈ ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ እስራኤል የሰላማዊ ዜጎችን አጠባበቅ ለማሻሸል እርምጃዎችን እንድትወስድ ከዚህ ቀደም ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ በጋዛ ያለው ሁኔታ እንደከፋ ሰብሳቢ ዳኛው ናዋል ሳላም ተናግረዋል።

እስራኤል ፍርድ ቤቱ ያቀረባቸውን ክሶች አጥብቃ በመቃወም ወታደራዊ ዘመቻዋን የሚያስቆም ማንኛውንም ውሳኔ እንደማትቀበል አመላክታለች።

ናዋፍ ሳላም “እስራኤል በራፋህ ግዛት እየፈጸመችው ያለውን ወታደራዊ ጥቃት እና ሌሎች ዘመቻዎች እንድታቆም እና የፍልስጤማውያንን ህይወት ከሚያወድም ማንኛውም እርምጃ ልታቆም ይገባል” ሲሉም የዘር ማጥፋት ወንጀል በአለም አቀፉ ህግ መሰረት ምን እንደሆነ በማጣቀስ አርብ ዕለት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አንብበዋል።

አክለውም እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለሚመረምር ማንኛውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ወደ ጋዛ እንዲገባ እንቅፋት ሳትፈጥር ልትፈቅድ ይገባል ብለዋል።

አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በዚህ ውሳኔው እስራኤል ለጋዛ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስን ጨምሮ ሰብዓዊ እርዳታዎች ባልተገደበ መልኩ እንዲገባ እንድትፈቅድ ያሳለፈውን የቀድሞውን ብያኔ እንደገና አስፍሯል።

“በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ የከፋ ቀውስ ውስጥ ነው” ሲል ነው ፍርድ ቤቱ በውሳኔው የፈረጀው።

እስራኤል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ከዓለም ህግ ጋር የተጣጠመ ነው ብለላች።

“እስራኤል በራፋህ አካባቢ ያሉ ፍልስጤማዊ ሰላማዊ ዜጎችን ኑሮ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ውድመት በሚያስከትል ሁኔታ እየፈጠረ ያለ ወታደራዊ ዘመቻ አላደረገችም እንዲሁም አታደርግም” ሲሉ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ዛቺ ሃኔግቤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ በበኩላቸው እስራኤል “ራፋህን ጨምሮ በየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ” ጥቃቷን እንደምትቀጥልበት ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ መንሱር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አድንቀው እስራኤል ብያኔውን እንድታከብር ጠይቀዋል።

“የአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን” ያሉት አምባሳደሩ አክለውም “ይህ ግዴታ ነው። እስራኤልም የጉባኤው አካል ናት” ብለዋል።