እስክንድር ነጋ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ከውሳኔ አልተደረሰም አሉ

እስክንድር ነጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፋኖ ታጣቂ ቡድን መሪ ከሆኑት አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ እስክንድር ነጋ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማድረግ ገና ከውሳኔ አልተደረሰም አሉ።

እስክንድር ነጋ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በንግግር ለመፍታት ከመንግሥት ጋር ሊደረግ ስለሚቻልበት ውይይትን በተመለከተ “ገና ከውሳኔ አልደረስንም” ብለዋል።

“ከመንግሥት ጋር እየተዋጉ ያሉ በርካታ የፋኖ ቡድኖች አሉ። እያንዳንዱ ቡድን እራሱን የቻለ ነው” ያሉት እስክንድር፤ በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የተለያዩ የፋኖ ቡድኖችን ለማዋሃድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

“በአሁኑ ወቅት አንድነት ለመፍጠር እየተነጋገርን ነው። ይህ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ከመንግሥት ጋር ሊደረግ ስለሚችል ድርድር ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል።”

እስክንድር ነጋ “በመርህ ደረጃ ድርድር ተቀባይነት ያለው ነገር ነው” ካሉ በኋላ፣ በአፍሪካ ያለውን ተሞክሮ በማንሳት ከብዙ የሰው እልቂት እና የንብረት ውድመት በኋላ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ድርድር ሲመለሱ ተመልክተናል ብለዋል።

“ለእኛ ጦርነት የመጨረሻው አማራጭ ነው። ብዙዎችን በመግደል እና በማፈናቀል ይህን ጦርነት የጀመረው መንግሥት ነው” ሲሉ ከሰዋል።

እስክንድር ነጋ ሲመሩት የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲ ጥለው ነፍጥ አንግበው ከመንግሥት ጋር መዋጋት ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል።

እስክንድር ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ ነፍጥ የማንገብ ትግልን የመረጡት “በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በማንነታቸው ምክንያት በመገደላቸው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያቸው በኃይል በመፈናቀላቸው ነው” ይላሉ።

የፌደራሉ መንግሥት እየተዋጋቸው ናቸው ከሚላቸው ታጣቂዎች ጋር አብሮ እየሠራ ነው በማለት የሚከሱት እስክንድር፤ “በእነዚህ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች ጥምረት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ እና ማፈናቀል ለማስቆም ጣልቃ መግባት የግድ ሆኖብናል” በማለት የትጥቅ ትግሉን ለምን እንደማራጭ እንደወሰዱት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቀት “80 ወይም 90 በመቶ የሚሆነው የአማራ አካባቢ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል” ያሉት እስክንድር፤ የመንግሥት ኃይሎች ዋነኛ ጥረት ሆኖ የቆየው በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ነው ይላሉ።

በአማራ ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መኖሩን ያስታወሱት እስክንድር፤ የፋኖ ኃይሎች ተቆጣጥረው በሚገኙባቸው አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች የሰብዓዊ እርዳታ ሥራ እንዲሰሩ ፍቃደኞች ነን ሲሉ ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት እንዲሁም የአማራ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በክልሉ፣ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በርካታ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

ከጥቂት ወራት በፊት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች በአማራ ክልል እየተፈጸመ ነው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ለተባበሩት መንግሥት ድርጅት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

እስክንደር ነጋም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን ጥያቄ በአንዎታዊ መልኩ እንደሚቀበሉት ገልጸው፤ በገለልተኛ ቡድን የሚደረግ ምርመራን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

“በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት ማስቆም ካስፈለገ መንግሥት በማንነታችን እኛን መግደል ማቆም አለበት። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በማንነታቸው ምክንያት ተገድለዋል። ሕዝብ ላይ የተከፈተውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ መቆም አለበት። ስር ነቀል ለውጥ መደረግ አለበት። ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ይኖርበታል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቀድሞ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ከፓርቲው መሪነት እና አባልነት መልቀቃቸው ከተነገረ በኋላ ፋኖን በመቀላቀል ወደ ትጥቅ ትግል መግባታቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት አቶ እስክንድር፤ በህትመት መገናኛ ብዙኃን ተሳትፏቸው በመቀጠል በመሠረቱት የፖለቲካ ፓርቲ ይታወቃሉ።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአማራ ክልል ይፋ የወጣው የመንግሥት ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ምክንያት ክልሉ ለአስር ወራት ያህል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንዲቆይ አድርጎታል።

አንድ ዓመት በሞላው አለመረጋጋት ውስጥ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተለያዩ መሪዎች ሥር የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች እንዳሉ ሲዘገብ የቆየ ሲሆን፣ እስክንድርም የአንዱ ቡድን መሪ መሆናቸው ይነገራል።

የፌደራሉ መንግሥት እና የአማራ ክልል አስተዳደር በክልሉ ለአንድ ዓመት የዘለቀውን ቀውስ በንግግር ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም እስካሁን ከየትኛውም ወገን የተሰማ ተግባራዊ እርምጃ ግን አልታየም።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአማራ ክልል በአራት የዕዝ ማዕከላት (ኮማንድ ፖስት) ሥር ተዋቅሮ የቆየ ሲሆን፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትም ወደ ክልሉ በይፋ ከተሰማራ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

አሁንም በበርካታ የአማራ ክልል አከባቢዎች ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች መቀጠላቸውን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።