በጊነስ በዕድሜ ትንሹ ተብሎ የተመዘገበው ህጻን ሠዓሊ

በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ህጻን ሠዓሊ ሊያም ከሥዕል ሥራው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

የምስሉ መግለጫ, በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ህጻን ሠዓሊ ሊያም ከሥዕል ሥራው ጋር

አንዳንዶች ከእናታቸው ማህጸን ተቀብተው ይወጣሉ የሚያስብሉ ክስተቶች በዓለማችን ይታያሉ።

ጨቅላው ኤስ-ሊያም ናና ሳም አንክራህ ለዚህ ማሳያ ከሆኑት አንዱ ነው።

ጋናዊው ሊያም ዕድሜው ገና አንድ ዓመት ከአምስት ወር ገደማ ቢሆነውም፣ ዓለም ትንሹ ሠዓሊ ተብሎ ዕውቅና ተሰጥቶታል።

በቅርቡም የዓለማችን ድንቃ ድንቆችን የሚመዘግዘበው ጊነስ ለሊያም ዕውቅና በመስጠት በመዝገቡ ላይ እንዲሰፍር ማድረጉ እናቱን ቃላት በሚያሳጥር ሁኔታ አስደስቷል።

የልጇ የጥበብ ችሎታ የሚያስገርማት አርቲስት እናቱ ዓለምን የሚያስደንቅ ሠዓሊ እንደሚሆን ተስፋዋ ከፍ ያለ ነው።

“እሱ ምን ዓይነት ቀለሞች እርስ በርስ እንደሚጣጣሙም ሆነ እንደሚደጋገፉ ያውቃል” ስትል ላለፉት ስምንት ዓመታት የጥበብ ሥራዎችን ስትሠራ የቆየችው እናቱ ቻንቴሌ ኩኩዋ ኢጋን ታስረዳለች።

እናቱ እንደምትናገረው የልጇን የሥዕል ችሎታ የተገነዘበችው ገና የስድስት ወር ልጅ እያለ ነው።

ጨቅላው ሊያም በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ትንሹ ሠዓሊ ተብሎ ለመመዝገብ ስድስት ወር መጠበቅ የነበረበት ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞም በይፋ ትንሹ ሠዓሊ የሚል ዕውቅና ተሰጥቶታል።

“ኢሜይሉን [ከጊነስ የተላከውን] ከፍቼ ሳነብ በእንባ ተሞላሁ፤ አምላኬን አመሰገንኩት” ስትል ልጇ መመዝገቡ የፈጠረባትን ስሜት እናት ለቢቢሲ አጋርታለች።

በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ህጻን ሠዓሊ ሊያም ከሥዕል ሥራው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

የምስሉ መግለጫ, ሊያም ከሌላ የሥልዕል ሥራው ጋር

ጊነስ ትንሹ ሠዓሊን በድንቃ ድንቅ መዝገብ እንዲሰፍር ለሕዝብ ክፍት የሆነ ዓውደ ርዕይ (ፕሮፌሽናል ኤግዚቢሽን) ማዘጋጀት ወይም መሳተፍ እንዲሁም የጥበብ ሥራዎቹንም መሸጥ አለበት የሚል መስፈርት አስቀምጦ ነበር።

በተጨማሪም የጥበብ ሥራዎቹ ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ መሠራት እንዳለባቸው እና ሥዕሎቹንም ራሱ ስለመሳሉ ማስረጃ መቅረብ አለበት ብሎ ነበር።

የሊያም ሥዕሎችን የያዘው ዓውደ ርዕይ በዚህ ዓመት ከታኅሣሥ እስከ ጥር መጀመሪያ ድረስ በጋና መዲና አክራ በሚገኘው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙዚየም ለዕይታ ቀርቧል።

ለዕይታ ከቀረቡት አስሩ ሥራዎች መካከል ዘጠኙ የተሸጡ ሲሆን፣ ዓውደ ርዕዩን የተመለከቱት ቀዳማዊት እመቤት ሬቤካ አኩፎ አዶ ሥዕል እንዲሥልላቸው ሥራ ሰጥተውታል።

በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ጨቅላው ሠዓሊ ሊያም በስድስት ወሩ

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

የምስሉ መግለጫ, በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ጨቅላው ሠዓሊ ሊያም በስድስት ወሩ

በሐምሌ ወር ሁለት ዓመት የሚደፍነው ድንቁ ሠዓሊ እስካሁን ባለው የሙያ ሕይወቱ 15 ሥዕሎችን ሸጧል፤ እንዲሁም በቅርቡ ጨረታ ሊያዘጋጅ አቅዷል።

ሊያም ወደ ጥበብ ዓለም የገባው ሳይታሰብ ነበር። እናቱ የሥዕል ሥራ እየሠራች ባለበት ወቅት እየዳኸ ነበር ወደ ቀለሙ የገባው።

ለሚስ ዩኒቨርስ 2023 ሥዕል እንድትሠራ ኮሚሽን ወስዳ እየሠራች ነበር። ልጇን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ከመሆኗ አንጻር የሥዕል ሥራዎቿን ስትሠራ ሊያምም በሆነ ነገር እንዲጠመድ ታደርገው ነበር።

በአንድ ወቅትም “ሥዕሌን እየሳልኩ ልጄንስ እንዴት መያዝ እና መንከባከብ እችላለሁ?” ስትል ራሷን ጠየቀች።

በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ጨቅላው ሰዓሊ ሊያም ከስዕል ስራው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

ብልሃት የተሞላበት ሃሳብ መጣላት። የሥዕል መሳያ ሸራ መሬት ላይ ዘርግታ ቀለሞች እንዲቀባ እና እንዲጫወትባቸው አደረገች። “ደማቆቹ ቀለማት ወዲያውኑ ነው የማረኩት፤ ሳቡት” ትላለች እናቱ በደስታ ስሜት።

ወዲያውኑም በቀለሞቹ መጫወት ጀመረ። የሥዕል ሥራዎቹም የተጠነሰሱት በዚህ መልክ ነው።

የመጀመሪያ ሥዕሉም “ዘ ክራውል” [የሚድኸው] የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። የሥዕል ሥራዎቹ አብስትራክት [ረቂቅ] የሚባለው የሥዕል አሳሳል ዘዬን የሚከተሉ ሲሆን፣ ደማቅ ቀለሞች የተሞሉበት እና አክሪሊክ የቀለም ዓይነትንም ይጠቀማል።

“ሥዕሎቹ ነገሮችን የማወቅ ፍላጎት ወይም ጉጉት ያለውን ሰው ያሳያሉ” ትለላች እናቱ ስለ ልጇ የጥበብ ሥራዎች ስትገልጽ።

በዓለም በትንሽነቱ በጊነስ የተመዘገበው ጨቅላው ሰዓሊ ሊያም ከስዕል ስራው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

እናት ልጇ የታዋቂውን ጋናዊ አርቲስት አማኮ ቦአፎን ፈለግ እንደሚከተል ተስፋን ሰንቃለች።

“አማኮ ከሥነ ጥበብ ጋር በተያያዘ ጋናን በዓለም ከፍተኛ ስፍራ ማስቀመጥ ችሏል” ብላለች።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ አርቲስቶቹ የአሜሪካዊው ጃክሰን ፖሎክ እና የእንግሊዙ ዴሚያን ሂርሰትን ሥራዎች እንዲያጠናም የእናቱ ምኞት ነው።

“ጃክሰን ፖሎክ በሽምግልናው ጊዜም ቢሆን ልጅነቱን ያልረሳ ነው፤ በሥራዎቹም ይንጸባረቃል። ሥራዎቹ ደማቅ እና የማይጠበቁ ዓይነት ናቸው። የልጄን ሥራ የማየው በዚህ መንገድ ነው” ስትል እናቱ ለቢቢሲ ገልጻለች።

ሊያም የጥበብ ችሎታውን ያሳድግ ዘንድ ዓለም አቀፍ የትምህርት ዕድል እንደሚያገኝም አርቲስት እናቱ ተስፋ አድርጋለች።

“ወላጆች የልጆቻቸውን ተሰጥኦ ከልጅነታቸው ጀምሮ በማየት እንዲያሳድጉት ማበረታታት እፈልጋለሁ” ስትል ምክሯን አስተላልፋለች።

ለልጇ የጥበብ ሥራ ማደግ ቆርጣ የተነሳችው እናት፣ ለልጇም ሥዕሎቹን የሚሠራበት የራሱን ስቱዲዮ ያዘጋጀችለት ሲሆን፣ ቀጣዩን ድንቅ ሥራውን ለመሥራት ዝግጁ ነው ትላለች።

  ጨቅላው ሰዓሊ ሊያም ከእናቱ እና ከጋና ቀዳማዊት እመቤት ሬቤካ አኩፎ አዶ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Chantelle Kuukua Eghan

የምስሉ መግለጫ, ጨቅላው ሠዓሊ ሊያም ከእናቱ እና ከጋና ቀዳማዊት እመቤት ሬቤካ አኩፎ አዶ ጋር