ኬንያ በአሜሪካ የኔቶ አባል ያልሆነች አጋር መባሏ ለቀጣናው መረጋጋት ምን ፋይዳ አለው?

ፕሬዝዳንት ሩቶ እና ፕሬዝዳንት ባይደን

የፎቶው ባለመብት, @POTUS

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሩቶ እና ፕሬዝዳንት ባይደን

ኬንያ የሰሜን አትላንቲን ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ያለሆነች አጋር የሚል ማዕረግ አግኝታለች። ይህን ስያሜ የሰጠቻት ደግሞ ኃያሏ አገር ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች ሰላም አስከባሪ ኃይል ሆነው ወደ ሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-አው-ፕሪንስ ሊያቀኑ እየተጠባበቁ ይገኛል። ኬንያ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደኅንነት ያላት ስም እየጎላ መምጣቱን እነዚህ እርምጃዎች ያሳያሉ።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በዋሺንግተን ታሪካዊ የተባለ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ። ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሩቶ፣ ስለሄይቲ ጉዳይ እንዲሁም ስሌሎች የሁለቱ አገራት ግንኙነቶች ውይይት አካሂደዋል።

ኬንያ አባል ያልሆነች የኔቶ አጋር በመሆን አራተኛዋ የአፍሪካ አገር ስትሆን ሰሀራ በታች አፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ ሆናለች። ይህ ማዕረግ ኬንያ በአፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ ሁነኛ ወዳጅ መሆኗን የሚያሳይ ሆኗል።

ዋሺንግተን በተባበሩት መንግሥታት ለሚታገዘው የሄይቲ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የሚሆን 200 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች። ኬንያ የቀጣናውን ሰላም በማስከበር ተነፃፃሪ ስኬት ያላት አገር ናት።

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በስምምነት የተረጋጋው በኬንያ መሪነት ነው። ከዚህ አልፎም ሩቶ በታላላቅ ሐይቆች (ግሬት ሌክስ) ቀጣና ያለውን መከፋፈል ለማርገብ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ የታየውን የአማፂያን መስፋፋት ለመግታት እየጣሩ ይገኛሉ።

በአውሮፓውያኑ ከ2001 ጀምሮ የኬንያ ጦር ሠራዊት በሶማሊያ አል-ሸባብ የተሰኘውን እስላማዊ ታጣቂ ቡድን እየመከተ ይገኛል። በኬንያዋ የላሙ ጠረፍ የሰፈረው የአሜሪካ ጦር ይህን ትግል እያገዘ ነው።

አሜሪካ የምትተማንበት አፍሪካዊ አገር ማግኘቷ እፎይታ ይሰጣታል። በተለይ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካ አገራት የምዕራባውያን ሚና እየቀነሰ መምጣቱ እና የሩሲያና ቻይና ተጽእኖ መበርታቱ አሜሪካን እንቅልፍ የነሳት ይመስላል።

ለፕሬዝዳንት ሩቶ ክብር የተካሄደ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, POTUS/fb

የምስሉ መግለጫ, ለፕሬዝዳንት ሩቶ ክብር የተካሄደ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት

ምን ለውጥ ያመጣል?

የምዕራባውያን የጦር ትብብር ማኅበር የሆነው ኔቶ አባል ያልሆነች አጋር የተባለችው ኬንያ፣ በጣም ዘመናዊ የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም ፀጥታዋን ለማጠናከር ሥልጣና እና ብድር ልታገኝ ትችላለች።

ነገር ግን ይህ ማለት አሜሪካ ለኬንያ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለባት ማለት አይደለም። ኬንያ በበኩሏ ለኔቶ ተልዕኮዎች ወታደር የመላክ ግዴታ አይኖርባትም።

ኬንያ በተደጋጋሚ ጥቃት ካደረሰባት አል-ሸባብ ቀጥተኛ አደጋ ቢደቀንባትም ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ጋር ሲነፃፀር ለወታደራዊው ኃይሏ የምትመድበው በጀት የጎላ የሚባል አይደለም።

ኬንያ እና ሶማሊያ በሚዋሰኑበት 680 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው ድንበር ላይ አነስተኛ የሚባሉ ጥቃቶች በደተጋጋሚ ይከሰታሉ።

አል-ሸባብ ኬንያ ውስጥ ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶችን አድርሻለሁ በማለት ኃላፊነት ወስዶ ያውቃል። በአውሮፓውያኑ 2013 መዲናዋ ናይሮቢ በሚገኝ ዌስትጌት በተሰኘ የገበያ አዳራሽ የተፈፀመው እና 70 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ይታወሳል።

ካለንበት የአውሮፓውያኑ 2024 መባቻ ጀምሮ አል-ሸባብ በኬንያ 30 ጥቃቶች ፈፅሚያለሁ ማለቱን ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ከቡድኑ መግለጫዎች ካሳባሰበው መረጃ ተገንዝቧል።

የቡድኑ አባላት ላሙ፣ ጋሪሳ፣ ዋጂር እና ማንዴራ በተባሉ የጠረፍ ከተሞች አካባቢ ይንቀሳቀሳል። በጥቃቶቹ አብዛኛውን ጊዜ ሰለባ የሚሆኑት የኬንያ ወታደሮች ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች በዓመቱ መጨረሻ ሶማሊያን ለቀው ለመውጣት ማቀዳቸውን ተከትሎ በኬንያ ድንበር አካባቢ ያላትን እንቅስቃሴ እያጠናከረች ነው።

አሁን የተሰጣት ማዕረግ ለመረጃ ስብሰባ እና ስትራቴጂካዊ ስምሪት ለማድረግ ሊጠቅማት እንደሚችል ይታመናል።

ኬንያ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ተልዕኮ ውስጥ መሳተፏ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አካባቢያዊ ሠራዊት ወታደራዊ ጥንካሬ የሚፈተንበት ነው።

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ተሰማርቶ የነበሩት ወታደሮች በዘጠኝ ወራት ለቀው መውጣታቸው እና አማጺያን እየተጠናከሩ መሄዳቸው የተልዕኮው ክሽፈት ማሳያ ነው ተብሎ ነበር።

ቢሆንም አሜሪካ ኬንያን ተጠቅማ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት ለማስፋፋት እና ግጭቶችን ለማብረድ የምታደርገውን ጥረት ቀጥላለች።

ምንም እንኳ አሜሪካ በቀጥታ ባትሳተፍም ፕሬዝዳንት ሩቶ 16 አሜሪካ ሠራሽ ሄሊኮፕተሮች እና 150 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሊሰጣቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከቀዳማዊ እመቤቶች ጋር

የፎቶው ባለመብት, POTUS/fb

የምስሉ መግለጫ, ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከቀዳማዊ እመቤቶች ጋር

የሄይቲ ተልዕኮ

ኬንያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ዘርፍ በሴራሊዮን እና በላይቤሪያ የዳበረ ልምድ ቢኖራትም፣ የሄይቲው ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይዝ በ2021 ከተገደሉ በኋላ ከ100 በላይ የታጠቁ ወንጀለኛ ቡድኖች መዲናዋ ፖርት-አው-ፕሪንስን የውጊያ አውድማ አድርገዋታል።

ሦስት መቶ ሺህ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ያደረገው ግጭት ጠቅላይ ሚኒስትር አሪዬል ሄንሪን በቅርቡ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ አስገድዷቸዋል።

የራሳቸውን ቀጣና ለማስመር እየተሯሯጡ ያሉት የሄይቲ ወንበዴዎች የጦር መሣሪያ በመግዛት እና በመሸጥ ላይም ተሰማርተዋል። አብዛኛው የጦር መሣሪያ ከአሜሪካ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገባ ሲሆን፣ ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ከጃማይካ እና ከኮሎምቢያም ይመጣል።

የተባበሩት መንግሥታት የዕፅ እና ወንጀል ቢሮ በዚህ ዓመት ባወጣው መግለጫ ወንበዴዎቹ የሩሲያው ኤኬ47፣ የአሜሪካው ኤአር15 እና የእስራኤሉ ጋሊል የተባሉ የጦር መሣሪያዎችን እንደታጠቁ አስታውቋል።

አሜሪካ ብዙ ልምምድ እና የጦር መሣሪያ ለሌላቸው የኬንያ ፖሊሶች ገንዘብ መመደቧ በከተማዋ ያሉ ወንበዴዎችን ለመቋቋም ሊያስችላቸው እንደሚችል ይገመታል።

ሌሎች የአፍሪካ አገራት ምን ይጠቀማሉ?

ከዚህ ቀደም አባል ያልሆኑ የኔቶ አጋሮች የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ እና ግብፅ ወታደራዊ አቅማቸው አስደናቂ የሚባል መሻሻል አሳይቷል።

በአውሮፓውያኑ 2015 ይህን ማዕረግ ያገኘችው ቱኒዚያ ወታደራዊ አቅሟ መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ ይህን ስያሜዋን ተከትሎ ወታደራዊ በጀቷን ከፍ ማድረግ ችላለች።

ከ1989 ጀምሮ የኔቶ አባል ያልሆነች አጋር የሆነችው ግብፅ በዓለማችን ካሉ ጠንካራ ጦር ሠራዊት ካላቸው አገራት ትመደባለች።

ግብፅ በሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ እንዲጨምር አስተዋፅዖ አድርጋለች።

የኢስላሚክ ስቴትስ (አይኤስ) ታጣቂዎች ጫና በርትቶባት የነበረችው ሞሮኮ በፀረ-ሽብር እንቅስቃሴው ያሳየችው መሻሻል ቀላል የሚባል አይደለም።

ሞሮኮ ከ2007 ጀምሮ በአፍሪካ ትልቁ የሚባለውን ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ሲሆን “አፍሪካዊ አንበሳ” የሚል ቅጽልም ተሰጥቷታል።

በዚህ ዓመት የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ ከ20 የአፍሪካ አገራት እና ከኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ ሰባት ሺህ ወታደሮች የሚሳተፉበት ይሆናል።