የሽግግር ፍትህ ኢትዮጵያን እስከ የት ያሻግራታል?

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ካጋደለ ሚዛን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን አጽድቋል።

የኢትዮጵያን አውድ መሰረት ያደረገ “የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት መዘርጋት” የፖሊሲው ዓላማ እንደሆነ ሰፍሯል።

“ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የህግ በላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበት መደላድል መፍጠር” ሌላኛው የፖሊሲው ዓላማ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።

የፖሊሲ ሰነዱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች (green paper) በባለሙያዎች ከተዘጋጀ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ነው።

ፖሊሲውን ለማርቀቅ በፍትሕ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውይይቶችን አካሂዷል።

እንዲሁም ከመጽደቁ በፊት የባለሙያዎች ቡድኑ በፖሊሲ አማራጮች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት በተመሳሳይ መልኩ ውይይቶችን አካሂዷል።

የባለሙያዎች ቡድኑ ከውይይቶቹ በኋላ የህዝብ ምክክር እና የግብዓት ማሰባሰብ ሂደት ሪፖርት ባለፈው ታህሳስ ወር ይፋ አደርጓል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ያጸደቀው ከእነዚህ ሂደቶች በኋላ ነው።

የፖሊሲው መግቢያ በ2010 ዓ.ም. በሀገሪቱ የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት “ለአለመግባባት፣ ለግጭት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ለተለያዩ የህዝብ ጥያቄዎች መፍትሔ ይሰጣሉ” ያላቸውን “የሕግ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አድርጓል” ይላል።

“ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት እና ከዚያም ቀደም ብሎ ባሉት ዘመናት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች አለመግባባቶች፣ ቅራኔዎች፣ ከባድ ግጭቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከስተዋል” ሲል ያክላል።

እነዚህን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች መደረጋቸውን ያስታወሰው ፖሊሲው ሙከራዎቹ “የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም” ይላል።

ፖሊሲው የተፈለገው መፍትሔ ያልተገኘው “በእውነት፣ በዕርቅ፣ በምህረት እና በፍትህ ላይ የተዋቀረ እና በግልጽ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች ሰብዓዊ መብት ተኮር በሆነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው” መሆኑን ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ባወጡት ጣምራ የምርመራ ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሊታዩ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትም በተመሳሳይ በጦርነቱ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማስፈን የፌደራል መንግሥቱ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ያትታል።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው የደም አፋሳሽ ጦርነት የተፈጸሙ እና በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጦር ወንጀሎች እና የዘር ማጽዳት ተብለው የተፈረጁ በዚህ የሽግግር ፍትህ የሚታዩ ይሆናሉ።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ይፋ የተደረገው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትችቶች እየቀረቡበት ይገኛሉ።

ከህግ ባለሙያዎች እና ከምሁራን ከሚቀርበው ትችት ባለፈ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሂደቱን ሲነቅፉ ተደምጠዋል።

ባለፈው ዓመት መጋቢት 2015 ዓ.ም. የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ላይ በተደረገ ውይይት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ረግጠው መውጣታቸው አንዱ ማሳያ ነው።

ፓርቲዎቹ በወቅቱ ከሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ በፊት “የሀገራዊ ምክክር ሊቀድም እና ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል” የሚል አቋም ይዘው ነበር።

የባለሙያዎች ቡድኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተቃውሞ ቢገጥመውም በ56 ከተሞች ግን የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶችን አድርጓል።

የሽግግር ፍትሕ “ከተጠያቂነት ለማምለጥ ወይስ አጥፊዎችን ለመቅጣት?’

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ልታደርገው እየተዘጋጀች ያለችው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከሚቀርብበት ትችቶች አንዱ “ተጠያቂነት ለማስፈን ዓላማ ያደረገ አይደለም” የሚል ነው።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ፤ “ከዓለም ዓቀፍ ጫና እና ማዕቀብ ማምለጫ ነው” ይላሉ።

ባለሙያው በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ላይ በርትቶባት የነበረው ጫና አሁን መለሳለሱን ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የማርቀቅ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ የምዕራባውያን ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማደስ ጀምረዋል።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ “የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ለቀጠናው መረጋጋት ቁልፍ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ ማድረግ እና ሀገሪቱን ማረጋጋት ይፈልጋሉ። አሁን የምናየው እንከን ያለበት የሽግግር ፍትሕ ሂደት፣ አንድ ዓይነት መሻሻል አለ በሚል ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደ ቀድሞ ለመመለስ ምክንያት ይሆናቸዋል” ይላሉ።

ሄግ በሚገኝ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ካሳሁን ሞላም “መንግሥት ይሄንን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የጀመረው ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማባበል ነው ወይም የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም ነው የሚል ክስ አለ” ይላሉ።

አቶ ካሳሁን ክሱ “ከመሬት ተነስቶ የቀረበ አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ።

“መንግሥት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመውን ወንጀል ለመርመር ለሚያደርጉት ጥረት [እና] የሚያወጡትን እውነቶች ለመሸፈን በሚመስል መልኩ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ አድርጓል” ሲሉ ለሚቀርበው ክስ ተጨባጭ ምክንያት መኖሩን ያስረዳሉ።

“[መንግሥት] ከባለሙያዎቹ ቡድን ጋር ለመተባባር ፈቃደኛ አልነበረም” የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ “ከዛም አልፎ ደግሞ የቡድኑን የጊዜ ቆይታ ለማቋረጥ ሲያግባባ ነበር።

ይሄ የሚያሳየው ምንድን ነው መንግሥት የተፈጸሙ ወንጀሎች እና ሀገሪቷ ውስጥ ያለው ሁኔታ ገለልተኛ ነጻ በሆነ አካል ወደ ውጭ እንዲወጣ ይፈልጋል ወይ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው” እንደሆነም ይናገራሉ።

በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው መርማሪ ቡድን የቆይታ ጊዜው ባለፈው ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይታወሳል።

የመርማሪ ቡድኑ የጊዜ ቆይታ እንዲራዘም ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አለመቅረቡን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወቀሳዎችን ሲያቀርቡ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ተቃውሞ ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን የቡድኑ የቆይታ ጊዜ እንዳይራዘም ተደጋጋሚ ጥረቶችን በማድረግ እንዲሁም በአገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ጥሰቶች ይታያሉ የሚሉ መከራከሪያዎች ማቅረቡ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰቶችን በብቃት መከላከልም ሆነ መርመር እንደተሳነው እና በምትኩ አካታች እና ግልጽነት የሚጎድለው ችግር ያለበትን የሽግግር ሂደት መጀመሩን በወቅቱ አመላክቶ ነበር።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሰብዓዊ መብት ባለሙያ መርማሪ ኮሚሽኑ እንዲዘጋ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ “የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትህ ሂደት ጀምሬያለሁ ማለቱ” እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ባለሙያው “የሽግግር ፍትህ ሂደት ተጀምሯል መባሉ የዓለም አቀፍ ውግዘቱን ቀንሶታል፤ ኮሚሽኑንም አዘግቷል። ይህ ለኢትዮጵያ መንግሥት ትልቁ ስኬት ነው” ይላሉ።

እንደ ሰብዓዊ መብት ባለሙያው “ይህ ለፍትህ ኪሳራ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ለፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተዋናዮች ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።”

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፖለቲካ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነችው ኬት ኦርኒን የሁለቱን ባለሙያዎች አስተያየት የሚያጠናክር ሃሳብ የያዘ መጽሃፍ ጽፋለች። ኬት “Hypocrisy and Human Rights Resisting Accountability for mass atrocities” በሚል ርዕስ በጻፈችው ድርሳን፤ “ የሰብዓዊ መብት ግዴታቸውን ለመወጣት ፈቃደኛ ያልሆኑ.... መንግሥታት ብዙ ጊዜ ለዓለም አቀፍ ጫና ምላሽ በሚያስደንቅ ሁኔታ አቋማቸውን ይለውጣሉ” ትላለች።

ኬት በዚሁ መጽሃፏ “መንግሥታት [ከዓለም አቀፍ] ቅጣት ለማምለጥ በቂ ነው ያሉትን ጥረት ብቻ ያደርጋሉ” የሚል ሃሳብ ታነሳለች። እንደ ኬት ገለጻ እነዚህ ጥረቶች በትክክልም የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመርመር የሚያስችሉ አይደሉም።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው ይህ የኬት ንድፈ ሃሳባዊ ትንተና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ይገልጻል ሲሉ ይሞግታሉ።

ባለሙያው “የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅጣት ለማምለጥ ከበቂም በላይ እየሰራ ነው” የሚሉት ባለሙያው የሽግግር ፍትሕ ሂደት መጀመሩ ግንኙነቶች ቀድሞው ወደነበሩበት እንዲመለሱ አድርጓል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ይሄን የሚያደርገው በመሰረታዊነት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ “[በሀገሪቱ] ፈላጭ ቆራጭነትም ሆነ ጦርነቱ እየቀጠለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍትሕን ለማስፈን ያቀደው አስተሳሰብ በቀላሉ የሚታመን አይደለም” ይላሉ።

ከዚህ ባሻገር የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ “አካታች አይደለም” የሚል ትችት ይቀርብበታል።

አቶ ካሳሁን ሞላ “[ሂደቱ] የግጭት መሪዎችን ወይም ደግሞ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ሰዎችን በተለይ ደግሞ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ [ቡድኖችን]፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪክ ማህበራትን አላካተተም” ሲሉ ይወቅሳሉ።

አቶ ካሳሁን አክለውም “እነዚህ ትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ በተለይ ደግሞ ግጭትን መምራት መቀስቀስ የሚችሉ አካላት ካልተሳተፉበት ዞሮ ዞሮ ወደሚፈለገው ውጤት ያመራል ማለት አስቸጋሪ ነው” ሲሉ የሂደቱ አካታች አለመሆን ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ያስረዳሉ።

ከሰባት ወራት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሽግግር ፍትህ ሂደቱ በፌደራል መንግሥቱ በብቸኝነት የተያዘ ነው በሚል ምክንያት ሂደቱን እንደማይቀበለው ማስታወቁን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።

አቶ ካሳሁን ይህ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ውድቅ ማድረግ የሚኖረው አንድምታ አሉታዊ መሆኑን “የትግበራው ሂደት ላይ ከትግራይ የሚመጣው ተቀባይነት እና አለመቀበል ተጽዕኖ ይኖረዋል”ሲሉ ይገልጻሉ።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ለፍትህ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፤ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት መሰረት ያላደረገ” መሆኑን ጠቅሰው ከፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ውይይት እንዲመቻች ጠይቀው ነበር።

በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ ይታያሉ ከመባሉ ጋር ተያይዞ ሌላኛው ከትግራይ በኩል የሚነሳው ትችት የጦርነቱ ዋነኛ ተሳታፊ የሆነው እና በተለያዩ የመብት ተቋማት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎችን ፈጽሟል የተባለው የኤርትራ ጦር ተጠያቂ የሚሆንበት ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውድቅ ማድረግ ለእኔ አስገራሚ አይደለም ምክንያቱም ለእነሱ ግልጽ የሆነላቸው አንድ ነገር አለ” ይላሉ።

ባለሙያው አክለውም፤ “ይሄ የሽግግር ፍትህ ሂደት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን ለተጠያቂነት ያቀርባል የሚል እምነት [ያላቸው አይመስለኝም]። የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን መርምሮ ተጠያቂ ያደርጋል የሚል እምነት የላቸውም ሊኖራቸውም አይገባም” ሲሉ ያብራራሉ።

“ይሄንን ሂደት መንግሥት ሙሉ በሙሉ በራሱ ይዞት ከሄደ ምናልባት ለፖለቲካ አገልግሎት ነው የሚያውለው” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ባለሙያው “የኢትዮጵያ መንግሥት ይሄን የሚያደርገው በመሰረታዊነት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው። የዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለማቋረጥ ነው ሌላ ዓለም አቀፍ የምርመራ ሂደቶች እንዳይጀመሩ ማምከኛ መንገድ ነው” ይላሉ።

በባለሙያዎች ትችቶች የሚቀርቡበት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚወደሰው የሽግግር ፍትህ ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።

ሚዛን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ለመሆኑ ምን ይዟል?

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ጠቅላላ ጉዳዮች፣ የፖሊሲ ጉዳዮች እና አቅጣጫዎች እና የመንግሥት እና የባለድርሻ አካላትን የሚዘረዝሩ ሶስት ክፍሎች አሉት።

የመጀመሪያው ክፍል የፖሊሲውን ዓላማ፣ መርሆዎች፣ የተፈጻሚነት ወሰን እና መሰል ጉዳዮችን የያዘ ነው።

የፖሊሲውን አብዛኛው ክፍል የሚሸፍነው እና ሁለተኛው ክፍል የወንጀል ተጠያቂነት፤ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባር፤ የምህረት፤ ማካካሻ፤ ተቋማዊ ማሻሻያ፤ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረግበት የጊዜ ወሰን የተመለከቱ አንኳር የሽግግር ፍትህ ስልቶችን ያቀፈ ነው።

ተግባራዊ የሚደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት “የወንጀል ምርመራ በማካሄድ እና ክስ በመመስረት አጥፊዎች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት የሚዘረጋ ይሆናል” ሲል ፖሊሲው ያትታል። ምርመራ እና ክስ የሚከናወነው “በጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ ያተኮረ” እንደሚሆን በፖሊሲው ላይ ሰፍሯል።

በፖሊሲው ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተብለው የተለዩት ወንጀሎች፤ “ስልታዊ፣ መጠነ ሰፊ ወይም ተከታታይነት (pattern) ባለው ሁኔታ የተፈጸሙ” ናቸው።

ፖሊሲው ምርመራ የሚከናወንባቸው እና ክስ የሚመሰረትባቸው አጥፊዎቹ የትኞቹ እንደሆኑም አስቀምጧል።

“ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር በሁሉም አጥፊዎች ላይ ምርመራ ማካሄድ እና ክስ መመስረት ተመራጭ አካሄድ አይሆንም” የሚለው የፖሊሲ ሰነዱ የምርመራ የሚከናወነው እና ክስ የሚመሰረተው፤ “ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ብቻ ይሆናል” ሲል ያትታል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ሌላው የሚዳስሰው ጉዳይ የወንጀል ምርመራ እና ክስ የሚከናወንበትን ተቋማዊ አሰራር ነው።

በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የሚከናወነው የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ተግባር የሚመራው ከዐቃቤ ህግ ተቋም ውጭ “ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ችሎ በሚቋቋም” ልዩ ዐቃቤ ህግ ተቋም ነው።

ምርመራ የማድረግ እና ክስ የመመስረት ስልጣን ራሱን ችሎ ለሚቋቋም ልዩ ዐቃቤ ህግ ቢሰጥም የፍርድ ሂደቱን ግን አሁን ባለው መደበኛ ፍርድ ቤቶች ስር በሚቋቋም ልዩ ችሎት እንደሚካሄድ ያስቀምጣል።

ፖሊሲውን ያረቀቁት ባለሙያዎች ፍርድ ሂደቱ “ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተለየ ራሱ አደረጃጀት የሚኖረው ነጻ እና ገለልተኛ ልዩ ፍርድ ቤት በህግ የሚቋቋም ይሆናል” የሚል ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ነገር ግን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፖሊሲውን ሲያጸድቅ የፍርድ ሂደቱን ለማከናወን በመደበኛው ፍርድ ቤቶች ስር “የተለየ የራሱ አደረጃጀት የሚኖረው ልዩ ፍርድ ቤት የሚደራጅ ይሆናል” በሚል አሻሽሎታል።

ይህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ፤ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል።

አቶ ካሳሁን “አሁን ባለው ሁኔታ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ ፍርድ ቤቶች ተዓማኒነታቸው በጣም አናሳ ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ ለመንግሥት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የተጋለጡ ናቸው” ይላሉ።

በፖሊሲው መሰረት የወንጀል ተጠያቂነት ተፈጻሚ የሚሆነው የሀገሪቱ ህገ መንግስት ከጸደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።

በጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊት ላይ የተሳተፉ ነገር ግን “ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ የሌላቸው አጥፊዎችን” በተመለከተ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው፤ “ሌሎች የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን በመጠቀም ጉዳያቸው የሚታይበት እና መፍትሔ የሚሰጥበት ስርዓት” እንደሚዘረጋ ያስቀምጣል።

እነዚህ ሌሎች የሽግግር ፍትህ ስልቶች ዕርቅ፣ እውነትን ማፈላለግ እና በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት ናቸው።

ፖሊሲው “እውነትን የማፈላለግ፣ ይፋ የማውጣት እና የዕርቅ ተግባራት ከተጽዕኖ እና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ በሚቋቋም አዲስ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነት እንዲከናወኑ ይደረጋል” ሲል ያትታል።

በዚህ ፖሊሲ አማካኝነት የሚቋቋመውን ኮሚሽን ጨምሮ ባለፉት አምስት ኣመታት ከዕርቅ፣ ሽግግር እና ምክክር ጋር የተያያዙ አምስት ኮሚሽኖች ተቋቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት የተቋቋሙት የዕርቀ ሰላም እና የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መሬት የወረደ ስራ ሳይሰሩ በህግ የተሰጣቸው የስራ ዘመን መጠናቀቁ ይታወሳል።

አሁን በስራ ላይ ያሉት የሀገራዊ ምክክር እና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የስራ ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ከአስር ወራት ያነሰ ጊዜ ነው የሚቀራቸው።

“ሁሉን አቀፍ አካታች ምክክር ያካሂዳል” የተባለለት የምክክር ኮሚሽን እስካሁን አጀንዳ መረጣውን አላጠናቀቀም። ቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ስልጣን የተሰጠው የተሃድሶ ኮሚሽንም ለስራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ፈተና ሆኖበታል።

ሰብዓዊ መብት ባለሙያው ይህ የኮሚሽኖች በተደጋጋሚ መቋቋም የሚኖረውን ተጽዕኖ “በተደጋጋሚ የሽግግር ኮሚሽኖች መቋቋማቸው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የወደፊት የሽግግር ሂደት ተነሳሽነቶች ቅቡልነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ ካሳሁን በበኩላቸው “አብዛኛውን ጊዜ የሚጀመሩት ኮሚሽኖች 'genuinely' [በእውነተኛ መልኩ] የፖለቲካው አውድ ካልፈቀደ እንደተባለው ለማስመሰል እና የዓለም አቀፍ ጫናን ለመቋቋም የሚደረግ ጥረት ነው የሚሆነው” ይላሉ።

አቶ ካሳሁን “አሁን ይቋቋማል የተባለው ኮሚሽን አሁን ባለው ሁኔታ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይችልም ልክ ከዚህ በፊት እንዳለፉት ኮሚሽኖች እዛው ተቀምጦ ስራውንም ሳይጀምር ጊዜው ሊያልቅ ይችላል” ሲሉ ያክላሉ።

ኬት ከላይ በተጠቀሰው መጽሃፏ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚታወቁ ሀገራት “ጥርስ አልባ ኮሚሽኖችን ይፈጥራሉ” ትላለች።

ሀገራት እነዚህን ኮሚሽኖች ቢፈጥሩም “የዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ጉብኝት ያደናቅፋሉ፣ እና በተመሳሳይ ጊዜ የመጨቆኛ አቅማቸውን እያጎለበቱ ትዕይንት ህግ ያወጣሉ” ስትል ታክላለች።

በፖሊሲው መሰረት ይህ አዲስ ኮሚሽን እውነትን ከማፈላላግ እና ይፋ ከማውጣት ባለፈ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት የመስጠት ኃላፊነትም ይኖረዋል።

ፖሊሲው “በጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች [ላይ] ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች የምህረት ተጠቃሚዎች አይሆኑም’ ሲል ምህረት የማይሰጥባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን አስፍሯል።

ማካካሻ ሌላኛው በፖሊሲው የተቀመጠው የሽግግር ፍትህ ስልት ነው። በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ኢፍትሀዊ አሰራሮች ምክንያት ተጎጂ የሆኑ ግለሰቦች እና ማህበረሰቦች የጉዳቶችን ዓይነት እና መጠን መሰረት በማድረግ በሚዘረጋ የማካካሻ ስርዓት እንደሚያልፉ ፖሊሲው ላይ ተቀምጧል።

እውነትን ማፈላለግ፣ ዕርቅ ማስፈን፣ እና ማካካሻ ስራዎች ዓላማ ፖሊሲው ተፈጻሚ የሚሆነው “መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ” እንደሚሆን ፖሊሲው ያትታል።

ፖሊሲው ይህ የሆነበት ምክንያት “ጥሰቶች እና ቅራኔዎች ከመሰረታቸው በማጥራት ለመመርመር፣ ስብራቶች እንዲሽሩ እና እንዲጠገኑ ለማድርግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲቻል” መሆኑን ያብራራል።

አቶ ካሳሁን ከላይ የተጠቀሱትን የሽግግር ፍትህ ስልቶች ለመተግበር “ግጭት እየተካሄደ ከሆነ እነዛን ስልቶች መተግበር እጅግ በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል” ይላሉ።

አቶ ካሳሁን አጠቃላይ የሽግግር ፍትህ በመንግሥት እጅ መሆኑ ሂደቱ ተዓሚነት ያለው እንዲሆን እና ዕውነተኛ ሽግግር እንዳይኖር ያደርጋል የሚል ስጋት አላቸው።

አቶ ካሳሁን ለዚህ መፍትሔ ይሆናል የሚሉትን ምክረ ሃሳብ “ለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የሚተገበሩት ሂደቶች ከመንግስት የፖለቲካ ተጽዕኖ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ራሳቸውን የቻሉ እና ነጻ ገለልተኛ የሆኑ ስልቶችን መተግበር የሚቻልበትን መንገድ መንደፍ ነው። አንደኛው መንገድ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሂደቱ እንዲካሄድ ማስቻል ነው” ይላሉ።

ዓለምአቀፍ ባለሙያዎች ወደ ሂደቱ እንዲገቡ የሚፈለገው “የሚፈለገውን ተዓማኒነት እና የሂደቶችን ነጻ እና ገለልተኛ መሆን ከመንግስት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነጻ መሆናቸውን ለማሳየት” መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው በበኩላቸው፤ ከሁሉም አስቀድሞ “ሰላማዊ የሆነ ፖለቲካ መደላድል ያስፈልጋል” ይላሉ።

በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ተዋናዮች “ከጦርነት ቀጠና የሚያወጣ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ መድረስ መቻል አለባቸው” የሚሉት ባለሙያው፤ “የሽግግር ፍትህ ‘relevant’ [ጠቃሚ] የሚሆነው የዛን ጊዜ ነው። የዛኔ የሽግግር ፍትህ ከተካሄደ የዲሞክራታይዜሽን [ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር] ሂደትን ሊደግፍ ይችላል” ሲሉ ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ።