የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለጣልያናዊው ታዳጊ የቅድስና ማዕረግ ልትሰጥ ነው

ቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ብላ ልትጠራው የተዘጋጀችው ታዳጊ ካርሎ አኩቲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢንተርኔትን በመጠቀም ስለ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመስበክ “የአምላክ ተጽእኖ ፈጣሪ” የሚል ስያሜ አግኝቶ ለነበረው ታዳጊ ቤተ ክርስቲያኗ የቅድስና ማእረግ ልስትሰጠው እንደሆነ ተገለጸ።

ቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ብላ ልትጠራው የተዘጋጀችው ታዳጊ ካርሎ አኩቲስ በአውሮፓውያኑ 2006 በካንሰር ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከአውሮፓውያኑ 1980 በኋላ ለተወለዱ፣ ‘ሚለኒያል’ ለሚባሉት ትውልድ የምትሰጠው የመጀመሪያ የቅድስና ማዕረግ ይሆናል።

የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ታዳጊው ያደረገውን ሁለተኛ ተአምር በቅርቡ እውቅና ሰጥተዋል።

በፍሎረንስ የዩኒቨርስቲ ተማሪ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከአንጎሉ ላይ ደም እየፈሰሰው የነበረ ቢሆንም የታዳጊው ተዓምር ፈውሶታል ተብሏል።

የካርሎ አኩቲስ ወደ ቅድስና ያስጠጋው የመጀመሪያው ተዓምር በአውሮፓውያኑ 2020 እውቅና የተሰጠው ነው። በጣፊያ ካንሰር ሲሰቃይ የነበረ አንድ ብራዚላዊ ታዳጊን የካርሎ አኩቲስ ተዓምር እንደፈወሰውም ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃ ነበር።

ሁለተኛው ተዓምር በፖፑ እውቅና የተሰጠው የቅድስና ማዕረግ ከሚሰጠው የቫቲካን ዲፓርትመንት ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላ ነው። ቅዱስ ተብሎ የሚሰየምበት ትክክለኛ ዕለት በቤተ ክርስቲያኗ አልተጠቀሰም።

ካርሎ አኩቲስ በደም ካንሰር ከተጠቃ በኋላ የልጅነት ጊዜውን ባሳለፈባት የጣሊያኗ ሞንዛ ከተማ ነው ህይወቱ ያለፈው።

የታዳጊው አስከሬን ያረፈበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ አስከሬኑ የጣሊያን ቅዱሳን በሚያርፉባት አሲሲ ከተማ ተወስዷል። በህይወት እያለ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሃይማኖታዊ መገልገያዎቹም በዚሁ ስፍራ ለሚገለገሉ ምዕመናን ክፍት ተደርገዋል።

በህፃንነቱ ቅዱስ ለሆነ ነገር ትልቅ ስፍራ ይሰጥ የነበረ መሆኑን እናቱ አንቶኒያ ሳልዛኖ ለኮሪ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተናግረው ነበር።

በብዙዎች ዘንድ የኮምፒውተር 'ጂኒየስ' (ሊቅ ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ታዳጊ ራሱንም ኮምፒውተር በህፃንነቱ አስተምሮም እምነቱን ለማስተማርና በርካታ የእምነት ድርጅቶችንም በመርዳት ይጠቀምበት ነበር።

ታዳጊው በበርካታ የእርዳታ ድርጅቶችም ተሳትፎ የነበረው ሲሆን ከራሱም ኪስ አውጥቶ አቅመ ደካሞችን ይረዳም ነበር።

"ባጠራቀማት ገንዘብ ቤት ለሌላቸው አቅመ ደካሞች ፍራሽና ብርድ ልብስ ይገዛ ነበር። ሲመሽም ትኩስ መጠጦችንም ይወስድላቸው ነበር" በማለት እናቱ ለካቶሊክ የዜና ወኪል ተናግራለች።

ከመሞቱም በፊት አስተምህሮቶቹን እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ያከናወነቻቸውን ተዓምራትን ዝርዝሮችን የያዘ ድረ ገጽ ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ ስራው ምክንያት “የአምላክ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚል ስያሜ ያገኘውም ከሞተ በኋላ ነው።

ድረገጹ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ማስተማሪያ ሆኗል። ተዓምራትን ለመመመር ወራት የሚወስድ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ ህግ መሰረት የቅድስና ማዕረግም ለማግኘት ቢያንስ ሁለት ተዓምራት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።