ፌስቡክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዜጐች አማፂያን 'እንዲቀብሩ' ያሳሰቡትን ጽሁፍ ሰረዘ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ግጭት ቀስቃሽ ቃላትን በመጠቀም የፌስቡክን ፖሊሲ ጥሰዋል በማለት ድርጅቱ የለጠፉትን ፅሁፍ አነሳ።

ባለፈው እሁድ ሕዝቡ መሳሪያውን በማንሳት የህወሓት አማጺያን እያደረጉት ያለውን ግስጋሴ እንዲያስቆም ጥሪ ያቀረቡበት መልዕክታቸው ነው ግጭት ቀስቃሽ የተባለው።

ፌስቡክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው ዓለም ይህንን የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም የሚደረጉ የጥቃት እና የግጭት ጥሪዎችን ማስቆም አልቻለም በሚል የተለያዩ ወቀሳዎችን እያስተናገደ ባለበት ወቅት ነው ይህንን እርምጃ የወሰደው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለጠፉት ፅሁፍ ላይ "አማጺ ቡድኑ እያደረገ ያለው ግስጋሴ አገሪቷን ወደ ጥፋት እየገፋ መሆኑን እና ሕዝቡም በመሰባሰብ እና በእጁ ያለውን ማንኛውንም ሕጋዊ መሳሪያ ወይም ኃይል በመያዝ ህወሓትን ለማስቆም እና ለመቅበር ይነሳ" ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ የለጠፉትን ፅሁፍ በተመለከተ ጥቆማዎች ከደረሱን በኋላ ፌስቡክ ጥቃት እና ግጭት ማነሳሳትን በተመለከተ ያለውን ሕግ የጣሰ ሆኖ ስላገኘነው እንዲነሳ ወስነናል" ሲሉ የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ድርጅታችን ሜታ የማኅበረሰብ መመሪያ ሕግጋቶቻንን የሚጥሱ ይዘቶችን ያነሳል፤ ግለሰቡ ማንም ይሁም ማን" ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ወር ከፌስቡክ ሾልኮ የወጣ ሰነድ ላይ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በታጠቁ ቡድኖች ግጭትን ለማነሳሳት እና አናሳ ብሔሮችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ መዋሉ ተጋልጦ ነበር።

ይህንን ምስጢራዊ ሰነድ ያጋለጠችው ፍራንሲስ ሐውሀን በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርባ ባብራራችበት ወቅትም ድርጅቱ "ፌስቡክ የብሔር ግጭቶችን በቀጥታ ሲያራግብ ነበር" ስትል ኢትዮጵያን በምሳሌነት በማንሳት ተናግራ ነበር።

በኢትዮጵያ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 ሲሆን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል በሚገኙ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ በሰጡበት ወቅት ነው።

መንግሥታቸው ይህን ያደረገው በአገሪቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን በአሸባሪነት ቢፈርጅም፤ ህወሓት በበኩሉ የትግራይ ክልል ሕጋዊ አስተዳዳሪ ነኝ ይላል።