Svoboda | Graniru | BBC Russia | Golosameriki | Facebook

በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮንግረስ አባላት ታይዋን ናቸው


የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች የልዑካን ቡድን ታይፔይ፣ ታይዋን
የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች የልዑካን ቡድን ታይፔይ፣ ታይዋን

የቻይና ጦር ኃይል ዛሬ ሰኞ ታይዋን አጠገብ ተጨማሪ የጦር ልምምዶችን ማካሄዱን አስታወቀ።

የቻይና የጦር ኃይል ልምምዱን ያደረገው ቀደም ሲል ላልተነገረ ጉብኝት ታይዋን የሚገኙ አሜሪካዊያን እንደራሴዎች ከፕሬዚዳንቱ ሳይ ኢንግ ዌን ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩበት በዚህ ወቅት ነው።

‘ታይዋን ግዛቴ ነች’ የምትለው ቻይና ጉብኝቱን ሉዐላዊነቷን የሚዳፈር አድራጎት እንደሆነ እየተናገረች ነው።

በዴሞክራቲክ ፓርቲው ሴኔተር ኤድ ማርኪ የተመሩት የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች ታይፔይ የገቡት ትናንት ዕሁድ ማታ ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ በቅርቡ ካደረጉትና የቻይናን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ካስከተለው ጉብኝት ጋር ሁለተኛው የኮንግረሱ ከፍተኛ ልዑካን ጉብኝት መሆኑ ነው።

የታይዋን አዋሳኝ አካባቢዎችን የሚቆጣጠረው የቻይና ምሥራቃዊ ቀጣና ዕዝ ዛሬ ታይዋን አካባቢ ባሉ የባህርና የአየር ክልሎች የጦርነት ዝግጅትና ልምምድ ማካሄዱን አስታውቋል።

“የጦር ልምምዱን ያደረግነው ዩናይትድ ስቴትስ እና ታይዋን "የቀጠሉት የፖለቲካ ተንኮልና የታይዋን ወሽመጥን ሰላምና መረጋጋት የማናጋት እንቅስቃሴ ለማስቆም ነው” ብሏል ዕዙ።

አምስት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ዛሬ፤ ሰኞ የታይዋንን ፓርላማ የጎበኘ ሲሆን ጉብኝቱ ራስ ገዟ ደሴት በአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ዘንድ ያላትን ድጋፍ ይበልጡን የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል።

ለኮንግረሱ ልዑካን አቀባበል ያደረጉት የገዥው የታይዋን ዴሞክራሲያዊ ተራማጅ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ሎ ቺንግ ቼንግ "ቻይና ወታደራዊ ልምምድ የምታደርገው የአሜሪካ እንደራሴዎች እንዳይጎበኙን ለማድረግ ቢሆንም ስለ ጉብኝታቸው ትልቅ ግምት እንሰጠዋለን" ብለዋል።

"የእንደራሴዎቹ ጉብኝት የየትኛውም ሀገር ልዑካን ታይዋንን እንዳይጎበኙ ቻይና መከልከል እንደማትችል የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ አሜሪካዊያን ከታይዋን ጎን እንዲቆሙ ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።

አሜሪካዊያኑ ልዑካንና የታይዋን ባለሥልጣናት በሚያካሂዱት ውይይት በባህር ወሽመጡ ላይ ያለውን ውጥረት ማርገብ፣ እንዲሁም ወሳኝ በሆነው የደሴቲቱ የኮምፕዩተርና ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች መረጃ መተንተኛና ማቀናጃ ግብዓት ወይም ቺፕ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ ነዋይ ማፍሰስን የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG