ጣልያን ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ምን ያህል ምቹ ናት?

ስደተኞች በጣልያን

በዕድሉ መንገሻ እና አበባ ተስፋዬ በተለያየ ጊዜ ከሱዳን ተነስተው፣ የሊቢያ በረሃን አቆራርጠው፣ የሜድትራኒያን ባሕር ሰንጥቀው ነበር ጣልያን የደረሱት። በዚያ ጉዞ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለው ፈተናን አይተዋል።

ጭው ባለ በረሃ የሰው ልጆችን አስከሬን ቅሪት እየተመለከቱ፣ እየተደበደቡ፣ እየተራቡ፣ እየተጠሙ እና በሕይወታቸው ‘እየቆመሩ’ የተመኟትን ጣልያንን ከረገጡ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ተስፋ ያደረጓት ጣልያን እንዴት ተቀበለቻቸው? ጣልያን ለኢትዮጵያን ስደተኞች ምን ያህል ምቹ ናት? የቢቢሲ ጋዜጠኞች ጣልያን በሄዱበት ወቅት በዕድሉ መንገሻ እና አበባ ተስፋዬን አግኘተዋቸው ታሪካቸውን አጋርተዋል።

★★★★

በዕድሉ መንገሻ አንዳንዴ ዕድሉን እያማረረ፣ ሌላ ጊዜ በዕድሉ እየተጽናና ነበር ጣልያን የደረሰው።

ወደ ጣልያን በሰሃራ በረሃ በኩል ሲሰደድ ብዙ ፈተና አይቷል።

ከሞት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል። ተደብድቧል። ታስሯል።

የሰው ልጅ የሚቋቋመው የማይመስለውን “መከራ ሁሉ” አይቷል።

እዚህ ሁሉ ላይ ውሃ ጥም፣ የበረሃ ንዳድ እና ርሃብ አለ።

“እኔ ስመጣ ይህንን መቋቋም አቅቷቸው የሞቱ ብዙ ልጆች አሉ” ይላል በዕድሉ።

አበባ ተስፋዬም በዕድሉ ያለፈበትን መንገድ አልፋበታለች።

መቀለ ተወልዳ በዚያው ከተማ እና ኤርትራ ያደገችው አበባ ጣልያን ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍላለች።

አበባ በልጀነቷ የወለደቻትን ልጅ ትታ “መጣሁ” ብላ ነበር ከቤት የወጣችው።

የሆነው ግን ሌላ ነው።

ወደ ቤቷ ለመመለስ፣ ልጇን ዳግም ለማግኘት ዓመታት ፈጅቶባታል።

አበባ ከቤቷ ስትወጣ ጣልያን በሀሳቧ ውስጥ አልነበረም።

ሌላ የኢትዮጵያ ከተማ ላይ ሠርታ ቤተሰቧን መርዳት ነበር የምታስበው።

አጋጣሚዎች ግን ወደ ሌላ አቅጣጫ ወሰዷት።

ራሷን ሱዳን ወስጥ አገኘችው።

መተማ ላይ ሻይ ቡና ስትሸጥ የነበረችው አበባ፣ ወደ ሱዳን ብትሻገር የተሻለ ገንዘብ እንደምትሠራ ሰዎች መከሯት።

ምክሩን ተገበረችው።

ወደ ሱዳን ተሻገረች። በዚያም የሰው ቤት ተቀጥራ ሠርታለች።

ሌላም ሥራ ሞክራለች። ነገሮች ግን አልጋ በአልጋ አልነበሩም።

ሱዳን ያሉ ሰዎች ደግሞ ከሱዳን ወደ ጣልያን “ብትሻገሪ ከዚህ የተሻለ ሕይወት ይገጥምሻል” አሏት።

አበባ አላመነታችም። ለተሻለ ሕይወት ተሰደደች።

“ጣልያን መግባት ለእኔ ህልም ነው። እኛ አካባቢ ሰው ያለው፣ ዘመድ ያለው ነው የሚሄደው። እንደዚህ እየተባልን ነው ያደግነው። ከጎረቤት ሰው ሲሄድ ወንድም አለው እህት አለው እየተባልን ነው የሚነገረን” ትላለች።

ጣልያን የመግባት ዕድል እጇ ላይ ወደቀ።

ሱዳን እየሠራች ለጉዞ የሚሆናትን ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረች።

ገንዘቧን ከፍላ ለጉዞ ስትዘጋጅ መጭበርበሯን አወቀች። “ደላሎቹ ገንዘቤን በሉኝ” ትላለች።

ተስፋ አልቆረጠችም እንደገና የጣልያን ጉዞዋን ጀመረች።

ጉዟዋን ለመቀጠል የሚያስችል በቂ ገንዘብ ስላልነበራት በሊቢያም ተቀጥራ ሠርታለች።

ከዚህ በኋላ መዳረሻዋን ጣልያን ለማድረግ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ጋር ጉዞ ጀመረች።

በጉዞዋ ከመታሰር ውጪ በዕድሉ የደረሰበትን ፈተና ሁሉ ቀምሳለች። ሴት በመሆኗ ምክንያት ደግሞ ሌሎች ፈተናዎችንም አይታለች።

ይህ የበርሃ ጉዞ የሰው ልጅ ሕይወት እጅግ የረከሰበት ነው።

ሞት ቀላል ነው።

የሰው ልጆችን የአስከሬን ቅሪት ማየት የማይገርም ነው።

አበባ መቼም የማትረሳው ነገር ገጥሟታል።

ጭው ባለ በረሃ ላይ “መሬት ላይ የተሰራ ዊግ አገኘሁ። እኔ የመሰለኝ እንደዚያ ነው። ሳነሳው ግን ከአሸዋው ስር የሰው ራስ ቅል ወጣ” ትላለች።

ይህ ለሕገውጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ምንም ነው።

አበባ ከእሷ ጋር ጉዞ ላይ የነበሩ ሁለት የሶማሊያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ተደብድበው ሲገደሉም አይታለች።

ሌላኛው ፈተና በተሽከርካሪ የሚደረግ ጉዞ ነው።

በዕድሉ በአነስተኛ የጭነት (ፒክአፕ) ተሽከርካሪ ነበር ያንን በረሃ ያቋረጠው።

በአንድ ተሽከርካሪ ላይ እስከ 30 ሰው ከዕቃ ጋር ይጫናል።

“ሰው ከወደቀ ላይቆሙ ይችላሉ። ጥለው ነው የሚሄዱት” ይላል።

አበባ በአንስተኛ ተሽከርካሪ ከ34 ሰዎች ጋር ተጭና ተስፋ ወዳደረገቻት ጣልያን ለመድረስ በበረሃ ስትጓዝ ነበር።

ይህንን የበረሃ ጉዞ የጨረሱ፣ የሜዲትራኒያንን ባሕር ለመሻገር ይዘጋጃሉ።

የሚሸጋገሩባቸው ጀልባዎች በሰዎች ብዛት አልያም በከባድ ማዕበል ምክንያት ችግር ሊገጥማቸው ይችላል።

በዚህ ጊዜ ስደተኞች በሕይወታቸው “ለመቆመር” ይገደዳሉ።

በዕድሉ እና አበባ ተስክቶላቸዋል። ባሕሩን አልፈው የጣልያንን ምድር ረግጠዋል።

ያልታደሉት የበረሃው አልያም የባሕሩ ሲሳይ ሆነዋል።

ለዚያ ነው በዕድሉ “የወደቀው እየወደቀ የተነሳው እየተነሳ ነው ጣልያን የሚገባው” የሚለው።

በዕድሉ በዚህ መንገድ ጣልያን ከገባ 18 ዓመታት ተቆጥረዋል።

አበባ ደግሞ 14ኛ ዓመቷን ይዛለች።

ስደተኞቹ ሕይወታቸውን አስይዘው፣ ተርበው፣ ተጠምተው፣ ተደብደበው እና ታስረው የተመኟትን ጣልያን አይተዋል።

ረብጣ ብሮች ለመሰብሰብ፣ ሕይወታቸውን ለመቀየር፣ ሠርቶ ሰው ለመሆን ተስፋ ያደረጓት ጣልያን ደርሰዋል።

ታዲያ፣ ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ ጣልያን እንዴት ተቀበለቻቸው? ጣልያን ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዴት ያለች አገር ነች?

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን፣ በጣልያን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስለሚገጥማቸው ሦስት ፈተናዎች ከደረሰባቸው፣ ካዩት እና ከሰሙት ተነስተው ነግረውናል።

አበባ ተስፋዬ ጣልያን ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍላለች።

የፎቶው ባለመብት, Abeba

የምስሉ መግለጫ, አበባ ተስፋዬ ጣልያን ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍላለች።

ቋንቋ እና ባህል

በዕድሉ አንድ ነገር አስተውሏል።

ጣልያን የሚገቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአገሬው ባህል እና ቋንቋ ጋር ለመላመድ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ወይም ሳይላመዱ ዓመታት ያልፋል።

“ቋንቋው ችግር ነው ቶሎ አንግባባም። ሀበሻው የሚኖረው ተመሳሳይ ቦታ እና ሕይወት ነው። ዞሮ ዞሮ ከጤፍ እና ከእንጀራ ጋር አንለያይም። የምንውለው እርስ በራስ ነው። ቋንቋ ለመልመድ ከሰው ጋር ለመላመድ ፈጣን አይደለንም። በእነሱ [በአገሬው ሰው] ዓይነት ሕይወትን ኖሮ፣ ያለውን ነገር ተጋፍቶ። ሕይወትን ለማሸነፍ አስቸጋሪ ነው” ይላል።

ይህንን ሀሳብ አበባም ትጋራዋለች።

“እኛ ቀኑን ሙሉ ከሀበሻ ጋር ነው የምንውለው . . . እግራችን እንጂ ጭንቅላታችን ከአገር አልወጣም። 20 ዓመት 30 ዓመት ኖረው ቀበሌ ወይም ለህክምና ሄደው ማነጋገር የማይችሉ አሉ። አሁንም በአስተርጓሚ ነው የሚነገርላቸው” ስትል ትገልጻለች።

ታዲያ ይህ እንዴት ችግር ይሆናል?

አበባ ቋንቋ ባለማወቅ ብዙ ኢትዮጵያውያን ግዴታቸውን ሳይወጡ ለችግር እንደሚዳረጉ ትናገራለች። ሕግ እና ደንቦችን ተላልፎ ለቅጣት ይዳረጋሉ።

መብታቸውን ለማስከበርም ፈተና ይገጥማቸዋል።

በሌላ በኩል፣ የስደት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚታሰበው ሥራ ጣልያንኛ ቋንቋን ሳይችሉ የሚታሰብ አይደለም።

በዕድሉ “ከውጪ እንደሚታየው አይደለም። እዚህ ተገብቶ ሲታይ አስቸጋሪ ነው። ለቋንቋው አዲስ ነን። መግባባት ሳይቻል ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል አይኖርም። አማርኛ የሚወራበት ቦታ ውለህ ጣልያን ቤት ሥራ መፈለግ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው” ይላል።

የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ባሕር አቋርጦ ጣልያን የገባው ኢትዮጵያዊ የጣልያንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ማግኘትም አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል።

ምናልባት ጣልያንኛ የሚከብድ ቋንቋ ይሆን?

ቋንቋውን አቀላጥፎ የሚናገረው በዕደሉ ይህንን ሃሳብ አይቀበለውም።

“ጣልያንኛ ቋንቋ የሚከብድ አይደለም። ደስ የሚል ነው። ሰዎቹም ይህንን ያህል የሚገፉ አይደሉም፤ እንዲያውም የራሳቸውን ምሥጢር ሁሉ ይነግራሉ። ግን [ቋንቋውን] ካልቻልክ ማንም ሰው አጠገቡ እንድትሆን አይፈልግም” ይላል።

ቀጥሎም “ቋንቋውን የለመዱ ሰዎች ከእኛም በፊት፣ ከእኛም በኋላ በደምብ ተግባብተው እየኖሩበት ነው፤ ቋንቋ አለማወቅ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ተግባብቶ ቶሎ በምትፈልገው ደረጃ ራስን ለማሸነፍ እንቅፋት ይሆናል” ይላል።

አበባም ነገሩ ገብቷት ቋንቋ እስከምታውቅ ድረስ ሥራ ለማግኘት እጅግ ተቸግራ ነበር።

በዕድሉ መንገሻ

የፎቶው ባለመብት, Bedlu

የምስሉ መግለጫ, በዕድሉ መንገሻ

የጠበቁት እና ዕውነታው

አበባ ጣልያን እንደገባች የጠበቀችው እና እውነታው ተጋጭተውባታል።

አበባ እና ሌሎች ስደተኞች ከጀልባ ላይ ፖሊሶች ያዟቸው። ወደ ጣልያን ግዛት ገቡ። ወዲያው አሻራ ሰጡ።

ብዙም ሳይቆዩ ስደተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ሰነድ ተሰጣቸው። “ከዚያ ‘ቻው’ ብለው አሰናበቱን” ትላለች።

ወደ ሮም በሚሄድ ባቡር ተሳፈረች። ሮም ግን የሚቀበላት፣ የሚያስጠጋት ሰው አላገኘችም።

አበባ የጣልያንን ምድር እስከምትረገጥ የጣልያን መንግሥት ቤት እንደሚሰጣት፣ ኑሮ አልጋ በአልጋ እንደሚሆንላት ነበር የምታስበው።

እውነታው ግን ሌላ ነው።

መውደቂያ ያልነበራት አበባ ሮም ላይ በሰው፣ በሰው፣ ሰው አገኘች። ያገኘችው ሰው ጣልያን “ትንሽ የቆየ” እና ቤት ተከራይቶ የሚኖር ነው።

“አሁን አሁን ነው ሰው [አገሩን] እስኪያውቅ ብለው መጠለያ የሚሰጡት እንጂ ያኔ አይሰጡም ነበር” የምትለው አበባ፣ ከዚህ ሰው ጋር ትዳር መሠረተች። መጠጊያ ብላ የመሠረተችው ትዳር ግን አልጸናም።

“የማይመች ሲሆን ጥዬው ወጣሁ። እርጉዝ ሆኜ ነው የተለየሁት” ስትል ትናገራለች።

ልጇን እስከትወልድ ድረስ መንግሥት መኖሪያ ቤት ሰጥቷት ነበር።

በዚህ መሃል ችግሯን ያዩ ሰዎች የሚወለደውን ልጅ በገንዘብ እንድትሰጣቸው ጠይቀዋታል።

“ብር እንሰጥሻለን ከዚያ ትፈርሚያለሽ ብለውኛል። ከዚያ ልጁ ጡት ሳይጠባ ነው የሚወስዱት። እኔ ግን እምቢ አልኩኝ” ትላለች።

ከወለደች ብዙም ሳትቆይ መንግሥት ካቀረበላት ቤት እንድትወጣ ተነገራት። መልሳ ከዚያ ችግር ጋር ተጋፈጠች።

በምናቧ የነበረችውን ጣልያን ምድር ላይ ማግኘት አልቻለችም።

ለ18 ዓመታት በጣልያን የቆየው በዕድሉ ጣልያን “ወርቅ የሚታፈስባት” እንዳልሆነች እና ላቡን ጠብ ላላደረገ ሰው ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ የተረዳው ወዲያው ነበር።

በዕድሉ በጣልያን ነዳጅ ማደያ ውስጥ መኪና አጥቧል፣ የጽዳት ሠራተኛ ሆኖ ሠርቷል።

ለአንድ ዓመት ሥራ አጥቶም “አካባቢውን በማየት እና በመዞር” አሳልፏል።

ከዚህ በኋላ በቫቲካን የአንጎላ አምባሳደር መኖሪያ ውስጥ ጽዳት፣ አስተናጋጅ እና ረዳት ምግብ አብሳይ ሆኖ 12 ዓመታትን አሳልፏል።

ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ምን አገኘ?

“እግዚያብሔር ይመስገን እስካሁን የሰው እጅ አላየሁም። ለችግር እጅ ሳልሰጥ ኖሬያለሁ። ሰው ሳላስቸግር ራሴን ችዬ እኖራለሁ” ይላል።

ነገር ግን ያኔ የተመኘው “ባለጸግነት” በስደት ኑሮ እንደማይሳካ ተረድቶታል። አገሩ ላይ ጥሪት ለማፍራት የሚያስችል እንኳን አቅም እንደሌለው ይገልጻል።

“ወደፊት አገሬ ላይ ቤት ሰርቼ ምናምን የሚለው ነገር ላይ አልደረስኩም” ሲል ያስረዳል።

ቀጥሎም “አሁን ልጆቼ እና ባለቤት ሌላ አገር ነው ያሉት። በማገኘው ደሞዝ ሦስት ልጆች ማስተዳደር በጣም በጣም ፈታኝ ነው” ይላል።

“ወደ ጣልያን ስመጣ ብዙ ነገር አስቤ ነው” የምትለው አበባ የጠበቀችው ነገር እጅግ የተጋነነ እንደነበር ብዙም ሳትዘገይ ተገንዝባለች።

በምናቧ የነበረችው ጣልያን ገንዘብ የተትረፈረፈባት ነበረች፤ እውነተኛዋ ጣልያን ደግሞ ሌላ።

ብዙ ‘የጉልብት’ ሥራዎችን የሠራቸው አበባ አሁን ላይ ሮም በሚገኝ አንድ የብሪታኒያ ሬስቶራንት በምግብ አብሳይነት እየሠራች ነው።

አሁንም የምታገኘው ገቢ ከዕለታዊ ወጪዋ አይዘልም። ገንዘብ መቆጠብ አይታሰብም።

“አሁን እኔ ስምንት ሰዓት ሰርቼ ወሬን ብቻ ነው የማሸንፋት። አንድ ወር ባልሠራ በለሁም ዜሮ ነው የምሆነው” ትላለች።

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አበባ እንደ በዕድሉ ሁሉ አገር ቤት ጥሪት ማስቀመጥ አልቻለችም። እንኳን ጥሪት ወደ አገር ቤት መመለስ ከባድ ሆኖባታል።

በ13 ዓመታት ውስጥ ወደ አገር ቤት የሄደችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

“ወደ አገር ቤት የሄድኩት በ2007 ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሼ አላውቅም። ለምን? - አልችልም። አቋራጭ ካላገኘሁ በስተቀር ሕይወቴን እቀይራለሁ ማለት አልችልም” ስትል ትገልጻለች።

የሥራ ክህሎት

“እኔ አንድ በራሴ ያስተዋልኩት ነገር አለ። ከኢትዮጵያ የምንሰደድ አብዛኞቻችን ሙያ የለንም” ይላል በዕድሉ።

በጣልያን የቧንቧም ይሁን የኤሌክትሪክ፤ የአውቶሞቢልም ይሁን የማሽን ሥራ፤ የልብስ ስፌትም ይሁን የጨርቃ ጨርቅ ሙያ ያለው ሰው “እጁን ተስሞ” እንደሚቀጠር ይገልጻል።

ችግሩ ሙያ ያለው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ጥቂት መሆኑ ነው ይላል።

“ከሌላ ቦታ የሚመጡ አብዛኞቹ ስደተኞች፣ ቢያንስ የሙያ ሰዎች ናቸው። በአካዳሚ ዕውቀት ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ኤሌክትሪክ፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ሙያዎችን ተምረው ነው ከአገራቸው የሚወጡት። እና እዚህ ሲመጡ ሥራ ለማግኘት አይችገሩም። እኛ ጋ ግን በጣም ጥቂት ሰው ነው ሙያ ያለው” ሲል ያስረዳል።

ለምሳሌ ይላል፣

“ልብስ ሰፊ እኛ አገር በጣም ብዙም ቦታ የሚሰጠው ላይሆን ይችላል፤ እዚህ ግን ጥሩ ሥራ ነው። አንድ ትንሽ የተቀደደ ልብስ ሰፍተህ 5 ዩሮ ነው የምታገኘው። በዚያ ሙያ እንኳን ኢትዮጵያዊ የለም። አብዛኞቻችን ሙያ ስለሌለን እዚህ ደርሰህ ሥራ ለማግኘት እጅግ በጣም እንቸገራለን።”

እኔ በመጣሁበት መንገድ ማንም ሰው እንዲመጣ አልመኝም የሚለው በዕድሉ፡

“ስደትን የሚያስብ ሰው አሜሪካም ይሂድ፣ ጣልያንም ይምጣ የትም ይሂድ፣ አገር ውስጥ የሙያ ባለቤት አልያም የዕውቀት ባለቤት ካልሆነ ሌላ ቦታ አገልግሎት አይሰጥም። አገር ውስጥ ባገኘኸው አጋጣሚ በሙያም ይሁን በአካዳሚ በአንድ ነገር ባለሙያ መሆን ይመረጣል። ባዶ እጅ ተሁኖ የተሻለ ነገር መጠበቅ አስቸጋሪ ነው” ይላል።