በዓለም ላይ ግዙፍ ገደሎች የመኖርያ መንደሮችን እየዋጡ ነው

ወደታች ያንሸራቱ

በድሮን የተቀረፀ የቡሪቲኩፑን ሸለቆ ቪዲዮ

በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዱ የሆነው ቡሪቲኩፑ ጎዳና በአንድ ወቅት በርካቶች የሚመላለሱበት ጎዳና ነበር

በድሮን የተቀረፀ የቡሪቲኩፑን ሸለቆ ቪዲዮ

አሁን ባለ 20 ፎቅ ሕንጻ መዋጥ የሚያስችል፣ 80 ሜትር ጥልቀት ያለው ሸለቆ ሆኗል።

በድሮን የተቀረፀ የቡሪቲኩፑን ሸለቆ ቪዲዮ

በአካባቢው ነዋሪዎች፣ የቱፒ ጉአራኒ ቋንቋ፣ እንዲህ ዓይነት ሸለቆዎች "ቮኮሮካ" ወይን "የተገመሰ መሬት" ይባላሉ።

በድሮን የተቀረፀ የቡሪቲኩፑን ሸለቆ ቪዲዮ

ይህ የ ሸለቆ መሸርሸር በዝናብ እና በፍሳሽ መልክ ከሚወገድ ውሃ የተነሳ የሚፈጠር የመሬት መሸርሸር ነው።

በድሮን የተቀረፀ የቡሪቲኩፑን ሸለቆ ቪዲዮ

በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ በከፍተኛ ፍጥነት እና በአስጊ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለ እና በርካታ ሺህ ቤቶችን እያወደመ ይገኛል።

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ጆሴ ሪባማር ሲልቬይራ በሸለቆው ውስጥ ወድቆ ከሞት አፋፍ ለጥቂት ነው ያመለጠው።

በ2023 ግንቦት ወር አንድ ምሽት ሲዝናና ከነበረበት ስፍራ ወደ ቤቱ ሲያሽከረክር መንገድ ስቶ ነበር።

የ79 ዓመቱ የቀድሞ ፖሊስ መኪናውን ጠምዝዞ ወደ ኋላ ማሽከርከር ጀመረ። ጨለማ ነበር፤ በቮኮሮካው አካባቢ የማስጠንቀቂያ ምልክት ወይንም ማገጃ አልነበረም፤ ምንም ነገር ከማወቁ በፊት መኪናው በግዙፉ ገደል ውስጥ ገባ።

"መኪናዋ ስትንሸራተት የወደቅኩት በፍጥነት ቢሆንም፣ ትንሹ ልጄ ነበር ወደ አእምሮዬ የመጣው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚህ አደጋ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሕጻን ጌይል አራት ወር ሞልቶት ነበር። አምላኬን ትንሹን ልጄን ማሳደግ እችል ዘንድ እንዲያተርፈኝ ለመንኩት" ይላል ሌተናል ሲልቬይራ።

በደረሰበት ከባድ አደጋ ራሱን ስቶ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሲነቃ፣ ከገደሉ ስር ነበር ራሱን ያገኘው። አስቸጋሪ ከሆነ የሕይወት አድን ሥራ እና ረዥም የማገገም ወራት በኋላ ያለ ክራንች መንቀሳቀስ ችሏል።

የጆሴ ሪባማራ ሲልቬይራ ምስል
ጆሴ ሲልቬይራ በገደሉ ውስጥ ከወደቀ በኋላ ከሞት አፋፍ ያመለጠው ለጥቂት ነበር

የእርሱ ገጠመኝ የቡሪቲኩፑ 70 ሺህ ነዋሪዎች የሚጋፈጡት አደጋ ግልጽ ማሳያ ነው።

በርካታ ሸለቆዎች በተፈጠሩ ቁጥር፣ ከአማዞን ጫካ አጠገብ የምትገኘው ማራናሆ ግዛት ለሁለት ይከፈላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። ከባሕር ጠለል በላይ 350 ሜትር ከፍታ ላይ በምትገኘው ቡሪቲኩፑ 30 ሸለቆዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ትልልቆቹ 1 ሜትር ርቀት ላይ ናቸው።

"ኃላፊዎቹ ይህንን መቆጣጠር ካልቻሉ፣ ተገናኝተው ወንዝ ይፈጠራል" ይላል ጂኦሎጂስቱ እና በማራናሆ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆነው ኢዲሊያ ዱትራ ፔሬይራ።

ሸለቆዎች ለሚሊዮን ዓመታት የመሬት ጂኦሎጂያዊ ታሪክ አካል ናቸው።

ነገር ግን ለፕሮፌሰር ፔሬይራ እና ላናገርናቸው ሌሎች ባለሙያዎች አሁን ያሉ ሸለቆዎች በፍጥነት እየሰፉ እና አዳዲሶች ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ ሊያስከትል በሚችል የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊፈጠሩ ይችላሉ ሲሉ ይሰጋሉ።

ማብራሪያ የተካተተባቸው የቡሪቲኩፑ ሳተላይት ምሥሎች

እንዲሁም ከተሞች ባልታቀደ ሁኔታ በሚስፋፉባቸው፣ የዝናብ ውሃን ለማስወገድ በቂ መሠረተ ልማት ባልተዘረጉባቸው አካባቢዎች ያለው አደጋ ይጨምራል።

ላቲን አሜሪካ ብራዚል በአስከፊ ሁኔታ የተጋለጠች አገር ብትሆንም፤ ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር እና አርጀንቲና በተመሳሳይ ችግር ተጠቅተዋል። ከአህጉሪቱ ባሻገርም በአፍሪካ እንደ አንጎላ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ናይጄርያ 2 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ሸለቆዎች ተፈጥረው ለአደጋ ተጋልጠዋል።

ለሸለቆዎች መሸርሸር ተጋላጭ የሆኑ የዓለማችንን ክፍል የሚያሳይ ካርታ

ይህ ዓይነት መሸርሸር በቻይና፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ለእርሻ ምቹ የሆነ መሬትን የሚያሰጋ ነው።

እዚህ ለመኖር በጣም አደገኛ ነው

ከሸለቆዎች ጋር የተያያዙ ሞቶችን የሚያሳይ መረጃ የለም፣ ነገር ግን የቡሪቲኩፑ ባለሥልጣናት ሸለቆዎቹ 50 ያህል ቤቶችን የዋጡ ሲሆን፣ አንዳንድ ነዋሪዎችም ቤታቸውን እና ቀያቸውን ጥለው ሸሽተዋል ብለዋል።

የማሪሳ ካርዶሶ ፍሬይሬ ቤት ከሸለቆው ጠርዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገሪቱ የአደጋ መከላከያ ተቋም በግንቦት ወር 2023 "ከፍተኛ ተጋላጭ" ተብሎ ተፈርጇል።

ከሌሎች 100 ቤተሰቦች ጋር ቤቷን ጥላ ወደ ሌላ የቡሪቲኩፑ አካባቢ መሄድ ይኖርባታል።

የከተማው አስተዳደር ለተፈናቃሉ ሰዎች የቤት ኪራይ ወጪን ለመሸፈን ቃል ገብቷል። ነገር ግን ማሪሳ አስተዳደሩ በወቅቱ የቤት ኪራይ አለመክፈሉን እና አከራዮቿ ሊያስወጧት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ትናገራለች።

ቢቢሲ የቡሪቲኩፑ ከተማ አስተዳደርን ባናገረበት ወቅት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

የማሪሳ ካርዶሶ ፍሬይሬ ምሥል
ማሪሳ ቤቷ መስመጡን አምና ለመቀበል ተቸግራለች።

በቀድሞው የማሪሳ ቤት ውስጥ የነበሩ ሁለት ውሾቿ ገደሉ ውስጥ ወድቀው ሞተዋል።

አንድ ቀን የ10 ዓመት ኦትስቲክ ልጇን፣ ኢንዞን፣ ለማግኘት ወደ ቤቷ መጥታ ጮኻ መጣራት ጀመረች።

ኢንዞ ተናድዶ ወደ ሸለቆው ጫፍ ሮጠ። "በድጋሚ ከጮህሽብኝ ራሴን ወደዚህ ሸለቆ እወረውራለሁ" ሲል አስፈራራት።

"ከዚያ በኋላ ነው ለባለቤቴ እዚህ መኖር የለብንም። በጣም አደገኛ ነው ስል የነገርኩት"
ማሪሳ ካርዶሶ

ምናልባት የገነባችው ቤት ውስጥ በጭራሽ መኖር ላትችል ትችላለች።

"ለቅቄ ስሄድ፣ ልቤን ሐዘን ክፉኛ ተጫነው፤ ምክንያቱም ይህ ቤት እንዲኖረን ጠንክረን ሠርተን ያገኘነው ነበር።"

እንዴት እዚህ ላይ ሊደርስ ቻለ?

ለእንዲህ ዓይነት የአፈር መሸርሸር የደን ጭፍጨፋ ትልቅ ድርሻ አለው።

ቡሪቲኩፑ አሁን ደረቅ ምድረ በዳ፣ ድንጋያማ ነው፤ ነገር ግን የአማዞን ጫካ አካል የሆነ እና በአንድ ወቅት በዛፎች የተሸፈነ ነበር።

በ1990ዎቹ የጣውላ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ በአካባቢው ተስፋፋ። 24 ሰዓት የሚሠሩ 50 ያህል እንጨት መሰንጠቂያዎች ነበሩ። ከ20 ዓመት በኋላ የከተማዋ የደን ሽፋን ተሟጦ አለቀ።

"አካባቢው በደን መሸፈኑ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በዝናባማ ወቅት መሬቱ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ይቀንሰዋል።"
ኢዲሊያ ዱትራ ፔሬይራ ጂኦሎጂስት እና በማራናኦ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር
ደን አልባ በሆነ አካባቢ ዝናብ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ የሚያሳይ አኒሜሽን

ዝናቡን መጥጦ ለማስቀረት የሚያስችሉ በቂ እፀዋት ወይም ዛፎች ሳይኖሩ ሲቀሩ. . .

በመሬት ላይ የሚገኝ ውሃ አኒሜሽን

የዝናብ ጠብታው የአፈሩን አካላት አልፎ በመግባት ውሃ እንዲያቁር ያደርጋል

ምንጮች ሲፈጠሩ የሚያሳይ አኒሜሸን

ምንጮች ተፈጥረው አፈሩን ጠርገው ይወስዱታል።

ሸለቆዎች ሲፈጠሩ የሚያሳይ አኒሜሽን

ሸለቆዎች ወይን ጉድባዎች ይፈጠራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ለሸለቆዎች መሸርሸር ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንዲኖር በማድረግ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ቡሪቲኩፑ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ከፍተኛ ነፋስ እና ነጎድጓድ የቀላቀለ ዝናብ እንደምታገኝ በማራንሆኦ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ጁአሬዝ ሞታ ፒንሄይሮ ይናገራሉ።

በ2023 የመጀመሪያ ወራት፣ የማራንሆኦ ግዛት በታሪክ አስከፊ የሆነውን ጎርፍ አስተናገደች። ከ60 በላይ ከተሞቿ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤት አልባ ሲሆኑ፣ በርካቶች ደግሞ ሞተዋል።

የቡሪቲኩፑ ሸለቆ
ይህ ሸለቆ በቡሪቲኩፑ ከሚገኙ 30 ያህል አንዱ ነው

"የዝናብ መጠን [በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ] በ10 እና 15 በመቶ እንደሚጨምር ትንበያው ያሳያል፤ ብዙ ላይመስል ይችላል፤ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን በተደጋጋሚ ካጋጠመ የአፈር መሸርሸሩ ሁኔታም በዚያው ልክ ይቀየራል" ይላሉ ቤልጂየም በሚገኘው ኬዩ ሌዩቨን የሚያስተምሩት ማቲያስ ቫንሜርኬ።

እርሳቸው እና ባልደረባቸው ዜን ፖይሰን በዓለማችን ላይ የሚገኙ የ700 ሸለቆዎችን መረጃ አጥንተው ከፍተኛ የዝናብ መጠን በዚያ ልክ ከጨመረ፣ የሸለቆዎችን መሸርሸር በሁለት እጥፍ ወይም በሦስት እጥፍ ይጨምረዋል ብለዋል።

"የአየር ንብረት ለውጥ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል በሚለው የምርምር ውጤት የማይስማማ ተመራማሪ ለማግኘት ያስቸግራል" ይላሉ ፕሮፌሰር ቫንሜርኬ።

የዝናብ ፍርሃት

ይህ ክስተት አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦችን የሚጎዳ ነው።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ በከተማዋ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስከ 2 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚረዝሙ ገደሎች አሉ። የ12 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ በሆነችው ከተማ ከ165 ኪሎ ሜትር በላይ ገደሎች ይገኛሉ።

የኪንሻሳ ገደል ምሥል
በ2021 በኪንሻሳ ሞንት ንጋፉላ ወረዳ የሚገኝ አውራ መንገድ ተደርምሶ ገደል ተፈጥሯል።

በታኅሣሥ ወር 2022 አንድ ምሽት በኪንሻሳ በዘነበ ከባድ ዝናብ የተነሳ፣ 60 ሰዎች ሲሞቱ ቤታቸው ደግሞ ተደርምሶ ገደል ተፈጠረ።

አሌክሳንድሬ ካዳዳ እዚህ ነበር።

"ከ30 እስከ 40 ደቂቃዎች ውስጥ ነው ሁሉ ነገር የተከሰተው። ገደሉ መከፈት ጀምሮ ሁሉም ቤቶች ሰምጠው ደብዛቸው ጠፋ፥ አካባቢው የማይታወቅ ሆነ" ይላል።

"ንብረቶቼ፣ ቤቴ፣ ሁሉም ነገር ደብዛው ጠፋ። ባለቤቴን እና ልጆቼን ብቻ ነው ማትረፍ የቻልኩት።"

ካዳዳ የሚኖርባት ሰፈር እና አራት ልጆቿ የአደጋው ሰለባ ከሆኑት መካከል ናቸው። ባለቤቷም የአካል ጉዳተኛ ሆኗል።

የካዳዳ ምሥል
አሌክሳንድሬ ካዳዳ የአደጋው ሰለባዎች አስተባባሪ ነው።

የካዳዳ ልጆች አየር ጠባይ ጥቂቱ ሲለወጥ እንኳ ፍርሃት ይውጣቸዋል።

"ዝናቡ ነው ሁሉ ነገራችንን ባዶ ያስቀረን። ዝናቡ ሞትን እና ሐዘንን ይዞብን መጣ" ይላል።

ፕሮፌሰር ቫንሜይርኬ "አንትሮፖሲን የዘመኑ የተፈጥሮ አደጋዎች አድርገን መቁጠር እንፈልጋለን" አንትሮፖሲን አንዳንድ ተመራማሪዎች የሰው ልጆች የሚያደርጉት ፕላኔቷን መጉዳቱን የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ክስተትን ለመሰየም የሚጠቀሙበት ቃል ነው።

በ2030 የኪንሻሳ ነዋሪዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፤ በ2050 ደግሞ 35 ሚሊዮን ደርሶ በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ከተሞች መካከል አንዷ ትሆናለች ሲል የዓለም ባንክ ትንበያ ያሳያል።

ቁጥጥር የማይደረግበት የከተማ እድገት ለአፈር መሸርሸር ተፈጥሯዊ መከላከያ የሆነውን የዛፎች መጨፍጨፍ እንዲሁም ምቹ ያልሆኑ ስፍራዎችን በሕገወጥ መልኩ መያዝን ያስከትላል።

ኪንሻሳን ከ2014 እስከ 2022 የሚያሳይ የሳተላይት ምሥል

በቡሪቲኩፑ ነዋሪዎች ዝናብን ይፈራሉ።

በአንድ ግዙፍ ገደል አቅራቢያ ጋራዥ ያላቸው የ52 ዓመቱ ዥዋአ ባቲስታ "አንድ ቤት የሚያክል መሬት የተደረመሰበት ጊዜ አለ፣ ሁሉን ነገር ነው የሚያናውጠው። ሰዎች ያለቅሳሉ። የሚያደርሰው የልብ ስብራት ያሳብዳል" ይላሉ።

"40 በመቶ ደንበኞቼን አጥቻለሁ። በርካቶች እዚህ መቆም ይፈራሉ" ይላሉ። ነገር ግን ለቅቆ ለመሄድ አይፈልጉም።

ከጋራዡ ጀርባ ያለው ቮኮሮካ ከዚህ በፊት የልጆች ኳስ መጫወቻ ሜዳ ነበር ይላሉ፣ ነገር ግን ሸለቆው ሁሉንም ነገር ዋጠው።

የዥዋኦ ባቲስታ ምሥል
ከባቲስቲታ ጋራዥ አጠገብ ያሉ ሌሎች ቤቶች ኦና ናቸው።

የአፈር መሸርሸሩን ለመቀነስ በማሰብ ቀርከሀ መትከል ጀምረዋል፥ ነገር ግን ከችግሩ ስፋት አንጻር፣ ቡሪቲኩፑ ከፍ ያለ መፍትሄ ትፈልጋለች።

ምን ሊደረግ ይችላል?

ፕሮፌሰር ቫንመየርኬ ነገር ግን ከትክክለኛው ምህንድስና እና መዋዕለ ነዋይ ጋር "ይህ ሁሉ ሊቆም የሚችል ነው" ይላሉ።

ፕሮፌሰር ፖይሴን የዝናብ ውሃውን እና የጎርፉን ፍሰት ለመቆጣጠር፣ የሸለቆዎቹ አፈር መሸርሸር ለማቆም፣ ለሸለቆዎች ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ውሃውን ለመቀልበስ ከተሞች ተገቢ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ መገንባት አለባቸው ይላሉ።

የቡሪቲኩፑ ሸለቆ ከ2004 እስከ 2023 የሚያሳይ የሳተላይት ምሥል

ይህ ግን በጀት አጠር በሆኑ ከተማዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሥራ ነው።

የማራንሆአ ግዛት ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የተስማማንበትን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ አተልጀመረም በማለት በቡሪቲኩፑ ከተማ ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተንቀሳቅሷል።

የቡሪቲኩፑ ከንቲባ ዥዋኦ ቴክሲየራ ዳ ሲልቫ በጉዳዩ ላይ አስተየየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፤ ነገር ግን የዝናቡን ውሃ መቀልበስ የሚያስችል ሥራ ለማከናወን ከፌደራል መንግሥቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የአገሪቱ መንግሥት 60 ሚሊዮን ዶላር ለቡሪቲኩፑ ከተማ ለመስጠት ማሰቡን ተናግሯል። የውሃ መውረጃ ቱቦዎች እና የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የተበላሹ መንገዶችን ለመጠገን እንዲሁም የፈረሱ 89 ቤቶችን ለመጠገን የሚውል 125 ሺህ ዶላር መልቀቁን አስታውቋል።

የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳለው ይህ ፕሮግራም "በከተሞች አደጋን የሚቋቋም ሥርዓት" ለመተግበር ያለመ ቢሆንም፣ ይህ ግን በአሁን ሰዓት በቡሪቲኩፑ ምንም እየፈየደ አይደለም።

"እጅግ ውስብስብ ሥራዎች ናቸው፣ ሥራዎቹ ከፍተኛ የሆነ ሀብት ይጠይቃሉ" ያሉት ከንቲባው ናቸው። "የምንፈልገው በከተማ እና በፌደራል ደረጃ ኃላፊነት እንዲኖር ነው።"

ነገር ግን ዦኣ ባቲስታ በጋራዡ ጀርባ የሚገኘው ገደል እየሰፋ መሆኑን አስተውሏል። ምናልባት ከዚህ ነቅሎ መሄድ ይኖርበታል።

"ተፈጥሮ ምድራችንን ካልተንከባከብን ልትጠፋ እንደምትችል እየነገረችን ነው። በዚህ ሁኔታ ዝናቡ የሚቀጥል ከሆነ፣ ዕጣ ፈንታችን ያለው በፈጣሪ እጅ ነው፤ ምክንያቱም ምንም ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም።"